ቀጥታ፡

በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች በመራጭነት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

 አዲስ አበባ መጋቢት 15/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች በመራጭነት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ጥሪ ቀረበ።

6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በሚመለከት የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተወጣጡ ሴቶች ጋር ውይይት አድርጓል።

የሊጉ ፕሬዘዳንት ወጣት ብርሃኑ በቀለ፤ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች በመራጭነትም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ምርጫው በሰላም እንዲከናውን በተለይ የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሞ፤ የውይይት መድረኩ ይህን ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ከዚህ ቀደም ምርጫውን በሚመለከት ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ሊጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠቱንም አስታውሷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሴቶች ምርጫን በሚመለከት ያላቸውን ፖለቲካዊ መብት በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አስያ አባተ እንዳሉት ሴቶች የሰላም እጦትና ፖለቲካዊ ቀውስ ሲፈጠር የመጀመሪያዎቹ ገፈት ቀማሾች ናቸው።

በመሆኑም ሴቶች በምርጫው ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።

ለዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ ከነገ መጋቢት 16 ጀምሮ ለአንድ ወር የመራጮች ምዝገባ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም