ቀጥታ፡

በዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2013 (ኢዜአ) በዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በታዛቢነት በንቃትና በብቃት በመሳተፍ፣ ለመራጮች ትምህርት በመስጠት እንዲሁም ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አሳሰበ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቀን አከባበር እንዲሁም በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድርጅቶቹ በሚኖራቸው ሚና ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡


የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት አዲሱ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች አዋጅ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ፤ በሰብአዊ መብት እና በምርጫ ጉዳዮች ላይ እንዳይሳተፉ በርካታ ማነቆዎች ነበሩ።

በተለይ ምርጫ ለአንድ አገር የዴሞክራሲ ስርአት ዋነኛ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሳካ እና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን የመንግስት የህብረተሰቡ ፤የምርጫ ቦርድ፤ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበራት ጥረትና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።


በምርጫ ቦርድ እውቅና የተሰጣቸውና በምርጫው ሂደት ተሳታፊ የሚሆኑ ሀገር በቀል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው ለመስራት ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ አቶ ጂማ አሳስበዋል።

በምርጫው በተለያየ መልኩ የሚሳተፉ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች በገለልተኝነት እንዲሰሩ ኤጀንሲው ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር ያደርጋልም ብለዋል፡፡


ማህበራቱ ህጋዊዩን መንገድ ብቻ ተከትለው በማይሰሩ ከሆነ ኤጀንሲው እርምጃ እንደሚወስድም አረጋግጠዋል።

ለዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።


በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቀን "የመንግስት፤ የሲቪክ ማህበራት፤ እና የግል ድርጅቶች ትብብር ለጋራ ልማታችን "በሚል መሪ ሃሳብ ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዚያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጀቶች ይከበራል።

እለቱን በማስመልከት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም የሚካሄድ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም