ቀጥታ፡

መንግስት በህደሴ ግድብ ዙሪያ እያራመደው ያለው አቋም የሚደነቅና የሚበረታታ ነው- ወጣቶችና ምሁራን

ደሴ መጋቢት 15/2013 (ኢዛአ) ''መንግስት ታላቁ የህዳሴ ግድብን ከነበረበት ችግር አላቆ ለታለመለት ግብ ለማብቃት የያዘው አቋም የሚደነቅና የሚበረታታ ነው'' ሲሉ የደሴ ከተማ ወጣቶችና የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትላንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሰጡት ማብራሪያ አንዱ በሆነው የህዳሴ ግደብ  ላይ የደሴ ከተማ ወጣቶችና ምሁራን አስተያታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል፡፡

የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ቢልልኝ ሙሄ እንዳለው መንግስት በህዳሴ ግድብ ዙርያ የያዘው አቋም የሚደነቅና የሚበረታታ ነው፡፡

መንግስት በግድቡ ግንባታና ውሃ ሙሌት ጨምሮ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ያደላትን ውሃ የመጠቀም መብቷን መከልከል ለሚሹ አካላት አስተማሪና ቁርጣቸውን እንዲያቁ የሚያደርግ መሆኑን ተናግሯል።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ህዝብ ወክለው አብረን እንጠቀም፤ ከጨለማ እንውጣ፤ ተመካክረን ችግራችን እንፈታ ማለታቸው የኢትዮጵያ የመረዳዳትና የመተባበር ባህል በተግባር ያሳየ መሆኑን ተናግሯል።

"ህዳሴ ግድቡ ከሁለንተና ችግራችን መላቀቂያ በመሆኑ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ሁሉም የየድርሻውን መወጣት አለበት" ያለው ወጣቱ በሀሳብ፣ በገንዘብና በጉልበቱ የሚችለውን ለማድረግ ዘግጁ መሆኑን አስታውቋል።

ሌላዋ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኢማን አሊ በበኩሏ" የህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያን ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያስተሳሰረ፣ የብሔር ብሔረሰቦች የአንድነት አርማ፣ የሁሉም አሻራ ያረፈበት፣ የድህነት መውጫ ብቸኛ መፍትሄ ነው " ብላለች፡፡

ግድቡ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ማድረግ አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሄ እንደሆነ ጠቅሳለች።

"ባለፈው ዓመት መንግስት ለህዝብ ቃል በገባው መሰረት ማንንም ሳይጎዳ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሊት በስኬት ማጠናቀቁ የሚደነቅና የሆዳሞችን ውሸት ከንቱ ያስቀረ  እንዲሁም  የአለምን ህዝብም ያስተማረ ነው" ብላለች፡፡

"መንግስት ዘንድሮም ፈተናዎችን ተቋቁሞ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሊት ከማካሄድ የሚያግደው እንደሌለ ጠንካራ አቋሙን ለአለም ህዝብ በማሳወቁ ኮርተናል፤ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግም አዘጋጅቶናል" ስትል ወጣቷ አመላክታለች።፡፡

ግድቡን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለማደናቀፍ የሚሰሩ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን እንደ አመጣጣቸው ለማስተናገድ መንግስትን መደገፍና ማበረታታት የወጣቱ የዘውትር ተግባር ሊሆን እንደሚገባ መክራለች።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና የአባይና አዋሽ ተፋሰሶች የምርምር ተቋም የውሃ ፖለቲካ አስተዳደር አስተባባሪ አቶ ጀማል ሰይድ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ ህዝብ ከጨለማና ከድህነት እንዲላቀቅ የህዳሴ ግድቡ በፍጥነት መጠናቀቅ አለበት" ብለዋል።

መንግስት የያዘው የማይነቃነቅ አቋም አበረታች፣ ወኔና ጉልበት የሚሰጥ፣ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት እንዲቆሙ የሚያደርግ፣ የኢትዮጵያን ምክንያታዊ፣ የእኩልና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በትክክል የሚገልጽ መሆኑን ተናግረዋል።

"የሐሰት ዘመቻ በመክፈት የግደቡን ግንባታ ለማጓተት የሚሰሩ ኃይሎችን መከላከል ይገባል" ያሉት ምሁሩ ምሁራን፣ አባቶች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ወጣቶች በተደራጀ አግባብ ድርጊቱን መከላከልና እውነታውን ለዓለም ማሳወቅ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

ግድቡን በተመለከተ መንግስት የያዘው አቋም የሚደነቅና የሚበረታታ በመሆኑ ሙሊቱ በእቅዱ መሰረት ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ በማንኛውም ጉዳይ ለሚደረግለት ጥሪ ድጋፍ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በህደሴው ግድብ የተጀመሩ ድርድሮች እንደተጠበቁ ሆነው የግድቡ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በቀጣዩ ክረምት የማይቀር ቁርጥ አቋም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሎ የመንግስትን አቋም ማሳወቃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም