ቀጥታ፡

የምርጫ ክርክሮች ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽና አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተጠቆመ

  አዲስ አበባ መጋቢት 15/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው ጠቅላላ መርጫ ላይ የሚፎካካሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክሮቻቸው ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡና አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት ተገለጸ።

ዘንድሮ የሚካሄደውን ምርጫ በሚመለከት ኢዜአ የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችን አነጋግሯል።

አመራሮቹ በሰጡት አስተያየትም በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የሚፎካካሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክሮቻቸው ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡና አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ ላይ ያተኮረ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ፓርቲዎች ትልቅ ሃላፊነት ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ ገመቹ እንደሚሉት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ አሸንፈው አገር ለመምራት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ፖሊሲያቸው ሊያስቀምጡ ይገባል።

ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ያሏቸውን አማራጮች ለህዝብ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ተድላ ኃይሌ በበኩላቸው የፓርቲዎች ክርክር ሕዝቡን እየፈተኑ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል በሚወሰዷቸው አማራጮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ፓርቲዎች ለህዝቡ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ግጭት የማይፈጥሩ፣ ሰላምና ልማትን ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተገኝ ዓለሜ ምርጫው የአገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ  የሚወስን በመሆኑ በጥንቃቄ መታየት አለበት ብለዋል።

የፓርቲዎች የምርጫ ክርክሮች ህፃናት፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ከግንዛቤ ባስገባና ሥነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ መሆን የኖርበታልም ነው ያሉት።

ፓርቲዎቹ አገራዊ ልማትን ከማፋጠን፣ ሰላምን በማስፈንና የአገሪቱን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ እንዲሁም የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ አተኩረው አማራጭ ሃሳቦቻቸውን ማቅረብ አለባቸው ብለዋል።

ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከምርጫ ደንብ ውጭ እንይሆኑ ሙያዊ አስተያየት በመሰጠት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋልም ነው ያሉት።

የሌሎች አገሮችን የምርጫ ተሞክሮዎችን ሙያዊ ዳሰሳ በማድረግ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለሚመለከታቸው አካላት ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ምሁራኑ ገልጸዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ እንዲሆን ምሁራኑ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም