ቀጥታ፡

የምርጫ ምልክት የወሰዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ጥሩ ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ እየተዘጋጁ ነው

 አዲስ አበባ መጋቢት 15/2013 (ኢዜአ) የምርጫ ምልክት የወሰዱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚችሉት አቅም ሁሉ በምርጫው ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገለጹ።

ለስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በርከት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን ውስደው ለሰላማዊ ፉክክሩ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ።

አስር ሳምንታት ለቀሩት የምርጫ ማከናወኛ ጊዜ የእጩዎች ምዝገባ የተጠናቀቀ ሲሆን የመራጮች ምዝገባ ደግሞ ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር ይከሄዳል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ካደረጉት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር በዝጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

የፓርቲው ተወካይ አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፤ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አንደኛው መሰረት መሆኑን ጠቅሰው የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የዚሁ ጥሩ ማሳያ እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል።

ሆኖም በየቦታው እየተከሰቱ ያሉ የጸጥታ ችግሮች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳደረባቸውም ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ፓርቲያቸው በምርጫው ላይ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርጫው ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል እድል ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይ 'የሕዝብ' ተብለው የሚታወቁ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አብዛኛው ከዚህ ቀደም የዘገባ ሽፋናቸው ላይ እኩል የማስተናገድ ችግር ነበረበት ሲሉም አንስተዋል።

በዘንደሮው ምርጫ ግን ለሁሉም ተፎካካሪዎች እኩል እድል ለመስጠት መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሳ አደም፤ ፓርቲያቸው በተሻለ መልኩ ለሰላማዊ የምርጫ ፉከከሩ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልላዊ ሆኖ የተመዘገበው የአፋር ሕዝብ ፓርቲ እስካሁን ባለው ሂደት እጩዎችን የማስመዝገብ፣ ማኒፌስቶውን ማስተዋወቅ ስራ መስራቱን ጠቅሰዋል።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ 96 ወንበር ለክልል ምክር ቤት እንዲሁም ስምንት ደግሞ ለፌዴራል የሕብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ለመያዝ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነም ነው የገለጹት።

አቶ ሙሳ እንደሚሉት ትልቁ የፖለቲካ ፓርቲያቸውን እየተፈታተነ የሚገኘው ችግር የመገናኛ ብዙሃን እጦት ነው።


በአፋር ክልል በቂ የመገናኛ ብዙሃን አለመኖሩንና የፌዴራል መገናኛ ብዙሃንን ለመጠቀም ደግሞ ለክልላዊ ፓርቲ አለመፈቀዱ ችግር ሆኗል ብለዋል።

በዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ 640 የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎችና 547 የተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ተደራጅተዋል።

ለ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከነገ መጋቢት 16 እስከ ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከናወን መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም