ቀጥታ፡

ኤዜማ ምርጫውን ካሸነፈ የብሔር ፌዴራሊዝምን በማስቀረት የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት የሚያሳድግ ስርዓት እንዲኖር ያደርጋል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

መጋቢት 14/2013 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ በምርጫ የመንግስትነት ስልጣን ከተረከበ የብሔር ፌዴራሊዝምን በማስወገድ የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት የሚያሳድግ ፌዴራላዊ ስርዓት እንዲኖር ያደርጋል ሲሉ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

ፓርቲው የምርጫ 2013 ዓ.ም የቃል ኪዳን ሰነዱን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

ፓርቲው በምርጫ ተወዳድሬ መንግስት መመስረት የምችልበትን ዕድል ካገኘሁ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል የምገባው ነው ያለውን የአምስት ዓመት የቃል ኪዳን ሰነድ የተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ ዘላቂ እድገትና አስተማማኝ ሠላም መፍጠር የሚያስችል የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ከብሄር ፖለቲካ መውጣት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ዜጎች በማንነታቸው ጥቃት ሲደርስባቸው የነበረውና አሁንም የቀጠለው ብሄርን መሰረት አድርጎ በፀደቀው ሕገ መንግስት ሲሉም ገልጸዋል።

መንግስት ሕግ ሲያወጣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጂ ለተወሰኑ ብሄሮች ወይም የሃይማኖት ተከታዮች ብሎ አይደለም፤ ይህ ደግሞ አገሪቷን ወደ ትርምስ ከቷታል ብለዋል።

ኢዜማ በምርጫ የመንግስትነት ስልጣን ከተረከበ ከሕዝቡ ጋር በመወያየት ሕገ መንግስቱ እንዲሻሻል ያደርጋል፤ የብሔር ፌዴራሊዝምን በማስወገድ የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት የሚያሳድግ ፌዴራላዊ ስርዓት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

'በኢትዮጵያ በብሄር የሚከሰቱ ችግሮችን በብሔር አደረጃጀት ለመፍታት መሞከር ስህተት ነው' ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከብሔር አደረጃጀት መውጣት አለበት ብለዋል።

በመሆኑም ኢዜማ ለሕዝብ ውይይት ያቀረበው የሕገ መንግስት ማሻሻያ ሀሳብ ተቀባይነት ሲያገኝ የክልል መንግስታትን አወቃቀር፣ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ ቋንቋ ባህልና ታሪክን የሃብት ስብጥርና ለብሔራዊ መግባባት አመቺ ሁኔታ መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ይሆናል ነው ያሉት።

መጪው የ2013 አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲኖራት ከማድረግ ባሻገር በሕዝብ የሚመረጠው መንግስት የሕዝቡን መሰረታዊ ችግሮች መፍታተ የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ 'በኢትዮጵያ የብሄር ፖለቲካው የበለጠ ሕዝባዊ መሰረት አለው?' ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ "ፍትሃዊና ተዓማኒ ምርጫ ተደርጎ የሕዝቡ ድምፅ ሳይሰማ ከዚህ ድምዳሜ መድረስ ስህተት ነው" ብለዋል።

የኢዜማ ብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ግርማ ሰይፉም የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት በራሱ ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ማሻሻል የሚቻልበት ዕድል አይኖርም ብለዋል።

በመሆኑም ኢዜማ ዛሬም ለዜጎች ግጭትና ለአገር ህልውና አደጋ የሆነውን ሕገ መንግስት ከሕዝቡ ጋር በመወያየት እንዲሻሻል ያደርጋል ብለዋል።

ኢዜማ የውጭ ግንኙነት ችግሮቻችን ውስጣዊ ችግሮቻችንን በአግባቡ ካለመያዝ የመነጩ መሆናቸውን ስለሚያምን በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲፈጠር ያደርጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም