ቀጥታ፡

የኢንጅነር ስመኘው በቀለ አስከሬን አሸኛኘት በመስቀል አደባባይ ተከናወነ

አዲስ አበባ ሐምሌ 22/2010  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የቀብር አሸኛኘት ስነስርአት በመስቀል አደባባይ ተካሄደ፡፡ ከማለዳው ሶስት ሰዓት ጀምሮ አስክሬናቸው በመኖሪያ ቤታቸው ጀምሮ አሸኛኘት እየተደረገለት ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ በመስቀል አደባባይ ይፋዊ የአሸኛኘት ስነ ሰርዓት ይደረግለታል ። በመቀጠልም ከቀን 7 ሰዓት ላይ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና መላው ህዝብ በተገኘበት የቀብር ስነ ሰርዓታቸው ይፈጸማል። የቀብር ስነ ስርዓቱ ለአንድ የልማት አርበኛ ጀግና በሚደረግ ስነ ስርዓት የሚከናወን ይሆናል። ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መስከረም 3 ቀን 1957 ዓ.ም በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ልዩ ስሙ ማክሰኝት በተባለ ቦታ ነው የተወለዱት። ከ1978 እስከ 1991 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ኮተቤ በሚገኘው ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አገልግለዋል። ከ1991 እስከ 1992 በኢንጂነሪንግ ክፍል በሲቪል ምህንድስና ሰርተዋል። ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ በግልገል ጊቤ ፕሮጀክት ያገለገሉ ሲሆን፤ የግልገል ጊቤ ሁለት ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን ሰርተዋል። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያዊያን የድካም ውጤትና ተስፋ በሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ኢንጅነር ስመኘው ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ማለዳ  መስቀል አደባባይ በሚያሽከረክሯት መኪና ውስጥ ተገድለው መገኘታቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም