ወቅታዊ የአየር ጠባይ ለውጥ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ ስልቶችን ቀይሼ እየሰራሁ ነው -- ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ

መጋቢት 14/2013 (ኢዜአ) የአየር ጠባይ ለውጥ መረጃን በየጊዜው ተደራሽ ለማድር የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ እየሰራ መሆኑን ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው ዓለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ቀንን "ውቅያኖስ የእኛ የአየር ጠባይና የአየር ሁኔታ" በሚል መሪ ሃሳብ አክብሯል፡፡

ዕለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ71ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ40ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ተቋሙ የአየር ጠባይ ለውጥ መረጃን በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ  በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው የመረጃ ማሰባሰቢያ መሳሪያዎችን በማዘመንና መረጃዎችን በፍጥነት ተንትኖ ተደራሽ እያደረገ ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን የብሔራዊ አየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍ ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

የሚቲዎሮሎጂ ጥናትና ምርምር በማካሄድ፤ የአየር ትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን በማከናወንና የምክር አገልግሎት በመስጠት የተሸለ ውጤት ለማምጣት እየሰራ ነውም ብለዋል፡፡

ዕለቱን አስመልክተው በበይነ መረብ አማካኝነት መልዕክት ያስተላለፉት የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ሴክሬታሪ ጄኔራል ፕሮፌሰር ፒተሪ ፓላስ በበኩላቸው ለአየር ጠባይ መለዋወጥ የውቅያኖሶች ሁኔታ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

40 በመቶ የሚሆኑ የዓለም ማኅበረስብ ክፍሎች በውቅያኖስ ዳርቻዎች አካባቢ በሚፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በመሆኑም በአየር ጠባይ ለውጥ ሳቢያ በውቅያኖስ አካባቢ የሚደርሰውን ተጽዕኖ መቀነስና ባህር አስተዳደር ላይ የተሻለ ስራ መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ አገራት በትብብር መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም