ሕዝቡ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝቡ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ተጠየቀ
መጋቢት 14/2013 (ኢዜአ) መላው ሕዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ጠየቀ።
የቦንድ ሽያጭ ሣምንት ማብሰሪያ መርሐ ግብር ዛሬ ሲጀመር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ200 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ ፈፅሟል።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ መርሐ ግብሩ በይፋ ሲጀመር ሕዝቡ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያደርገውን ተሳትፎ ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።
ሕዝቡ እስካሁን ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለው ጥረትና ተነሳሽነት የሚደነቅና የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
በግድቡ ዙሪያ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሳያዘናጋው በባለቤትነት ስሜት ግንባታውን ለማጠናቀቅ ጥረቱን መቀጠል እንዳለበትም ነው ያመለከቱት።
ሕዝቡ በተሳትፎው ግንባታው 79 በመቶ የደረሰውን ግድብ 'እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን' በሚለው መርሁ ከፍጻሜ እንዲያደርሰው ነው ዶክተር አረጋዊ የጠየቁት።
ኅብረተሰቡ ሳምንቱን ምክንያት በማድረግ ቦንድ በመግዛትና በስጦታ እንዲያበረክት ጥሪ ያደረጉት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፍቅረሥላሴ ዘውዱ ናቸው።
ባንኩ በመርሃ ግብሩ መጀመሪያ ቀን የ200 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ መፈጸሙን ገልፀው፤ ባለፉት ዓመታት ሠራተኞቹን በማስተባበር አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ፍቃዱ ደግፌ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ 10ኛ ዓመት በሚከበርበትና በግድቡ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅት ሳምንቱ መዘጋጀቱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የቦንድ ሽያጩ በሁሉም ንግድ ባንኮች፣ በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ለዚህም ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ጊዜያዊ የመሸጫ ድንኳኖች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ኅብረተሰቡ ከ50 ብር ጀምሮ ለግዥ የቀረቡትን ቦንዶች እንዲገዛም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ ሕዝቡ ለአገሪቷ ልማት የሚያስፈልገውን ኃይል ለማሟላት በግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ረዳት ትራንዚተሮች ማኅበር የ100 ሺህ ብር ቦንድ ገዝቷል።