ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማዕድንና ነዳጅ ምህንድስና ትምህርቶችን በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ለማስተማር ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2013/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማዕድንና ነዳጅ ምህንድስና ትምህርቶችን በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታወቀ።

የትምህርቱ መጀመር ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ሃብት በአግባቡ አንድትጠቀም እንደሚያግዛትም ነው የተገለጸው።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዴኤታ ስመኝ ውቤ በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ በቂ የሰለጠነ የሰው ሃይል ባለመኖሩ ምክንያት 'ያለንን ሃብት በተገቢው ልክ ሳንጠቀምበት ቆይተናል' ብለዋል።

ሜኒስቴር መስሪያ ቤቱ ችግሩን ለመቅረፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ትብብሩ በተለይ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ለማስተማር መዘጋጀቱ የዚህ ጥረት አካል መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ በተቋሙ የሚሰሩ 50 ባለሙያዎች ወደ ትምህርት እንደሚገቡ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ አሰፋ ዘርፉን ለማበልጸግ "የማዕድን ምህንድስና" እና "ነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች ምህንድስና" የሚሉ ሁለት የትምህርት ዘርፎች መቀረጻቸውን ገልጸዋል።

የትምህርት ምክር ቤቱ የትምህርት ስርዓቱን ገምግሞ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት እንዲያፀድቀው ማቅረቡንም ተናግረዋል።

ትምህርቱን በሁለት ወራት ውስጥ ለማስጀመር ከወዲሁ 50 በዘርፉ የተሰማሩና ተቀራራቢ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ሰልጣኞች  መመልመላቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

በቀጣይ አስርት ዓመታት 675 ባለሙያዎችን በዘርፉ ለማሰልጠን ዕቅድ መያዙንም ዶክተር ብርሃኑ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች አጫጭር ስልጠና ይሰጣል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም