የመንግሥት ሠራተኞች ለኢትዮጵያ መጻኢ ሠላምና አገረ-መንግሥት ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት ሠራተኞች ለኢትዮጵያ መጻኢ ሠላምና አገረ-መንግሥት ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ መጋቢት 14/2013 የመንግስት ሠራተኞች በአገራዊ ምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለኢትዮጵያ መፃኢ ሠላምና አገረ -መንግስት ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።
ኢዜአ የሲዳማ፣ የሐረሪና የጋምቤላ ክልሎች የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ሃላፊዎችን ምርጫውን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ጠይቋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ሥርዓት ከመገንባት ባሻገር ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን ፈተና ለማለፍና ጠንካራ አገረ-መንግስት ለመገንባት ከፍያለ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።
ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥና የኢትዮጵያን መፃኢ ዕጣ-ፈንታ ለመወሰን ደግሞ በተለይ የመንግስት ተቋማት ሠራተኞች በምርጫው ነጻና ገለልተኛ ሆነው ሊሳተፉ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ምርጫው ካለፉት ምርጫዎች በተለየ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ለሌሎች አገራትም ምሣሌ እንደሚሆን ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
የሲዳማ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ምክትል ቢሮ ሃላፊ ዮካም ዮዬ፡-"ከየትኛውም ሠላምን ከሚያውኩ፣ የምርጫ ሂደቱን ከሚበጠብጡ ተግባሮች ራሱን መጠበቅ፣ እንዳለበት አሳስበዋል።
የሐረሪ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ሁንዴ፡-ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ ከመንግስት ሠራተኛው ብዙ ነገር ይጠበቃል፤ በምርጫው ተሳታፊ መሆን እና የሚፈልጉትን ፓርቲ በነጻነት መምረጥ አለባቸው።
የጋምቤላ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ሃላፎ አቶ ተንኩዌይ ጆክ ሮም፡-ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዴሞክራቲክ እንዲሆን የመንግስት ሰራተኞች በንቃት እንዲሳተፉ ጠይቀዋ።
የፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ በበኩላቸው የመንግስት ሠራተኛው በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ መሳተፍ እንዲችል በሁሉም ክልሎች ውይይቶች ተካሂደዋል ብለዋል።
የመንግሥት ሠራተኛው ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ በአገረ-መንግስት ግንባታው ንቁ ተሳታፊ በመሆን ላመነበት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፁን በመስጠት የዜግነት ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ዝግጅቶች እያደረጉ ነው።
በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ከየካቲት 8 ቀን 2013 ጀምሮ ማካሄድ የጀመሩ ሲሆን እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ይቀጥላል።
መራጮችም ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጻቸውን ላመኑበት የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።