የኢንጅነር ስመኘው በቀለ አስከሬን በመኖሪያ ቤታቸው አሸኛኘት ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
የኢንጅነር ስመኘው በቀለ አስከሬን በመኖሪያ ቤታቸው አሸኛኘት ተደረገለት
አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2010 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ አስከሬን በመኖሪያ ቤታቸው አሸኛኘት ተደረገለት። ኢንጂነር ስመኘው ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው የሚታወስ ነው። በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገው የአስክሬን አሸኛኘት ሥነ ስርአት የሃይማኖት አባቶች ጸሎትና ፍትሐት ያደረጉ ሲሆን፤ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውንና በስፈራው የተገኙ ሐዘንተኞችን አጽናንተዋል። የኢንጅነር ስመኘው አስከሬን ለምርምራ ከተላከበት ከጳውሎስ ሆስፒታል ትናንት ከሰዓት በኋላ ነው ወደ መኖሪያ ቤት የተመለሰው። አስክሬናቸው ወደ መስቀል አደባባይ የሚያመራ ሲሆን፤ በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀው ልዩ የሽኝት መርሃግብር ማንኛውም ሰው በመገኘት ሃዘኑን መግለጽ እንደሚችል የብሔራዊ የቀብር አስፈጻሚው ኮሚቴ ትናንት ማምሻውን አስታውቋል። የኢንጀነር ስመኘው በቀለ የቀብር ሥነ ስርዓት ዛሬ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከቀኑ በሰባት ሰዓት ይፈጸማል። ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መስከረም 3 ቀን 1957 ዓ.ም በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ልዩ ስሙ ማክሰኝት በተባለ ቦታ ነው የተወለዱት። ከ1978 እስከ 1991 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ኮተቤ በሚገኘው ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አገልግለዋል። ከ1991 እስከ 1992 በኢንጂነሪንግ ክፍል በሲቪል ምህንድስና ሰርተዋል። ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ በግልገል ጊቤ ፕሮጀክት ያገለገሉ ሲሆን፤ የግልገል ጊቤ ሁለት ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን ሰርተዋል። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያዊያን የድካም ውጤትና ተስፋ በሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።