ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ከባህሏ ለይቶ ማየት መልክዓ ምድርን ብቻ መመልከት ነው ...ምሁራን

ሚዛን፤መጋቢት 14/ 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ከባህሏ ለይቶ ማየት መልክዓ ምድርን ብቻ መመልከት በመሆኑ ባህላዊ እሴቶቻችንን በመጠበቅ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል ሲሉ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ገለጹ።

በሀገሪቱ እየታየ ያለው የመከፋፈልና የሰላም እጦት በባህል መሸርሸር የመጣ መሆኑን ምሁራኑ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩንቨርስቲ የስነሰብ መምህር አበጀ መንበሩ እንዳሉት ማህበረሰብና ባህል አንድ ላይ የተቆራኙና የማይነጣጠሉ ናቸው።

የኢትዮጵያን ህዝብ ከባህል ለይቶ ማየት አይቻልም ያሉት ምሁሩ የበርካታ ብሔረሰቦች መኖርያ እንደመሆኗ በዚያው ልክ ያላት ቱባ ባህል ከምንም በላይ  ህዝቦቿ በሰላምና አብሮነት እንዲኖሩ ያደረጋት መሆኗን ገልጸዋል።

"ስርዓትና ወግ የሚያስጠብቁ የብዙ ሃይማኖትና እሴቶች ባለቤት የሆነች ኢትዮጵያን ከባህሏ ለይቶ ማየት መልክዓ ምድርን ብቻ መመልከት እንጂ ሀገርን ማየት አያስችልም" ብለዋል።

ባህላዊ እሴቶቻችን የሆኑ የግጭት አፈታትና የእርቅ ስነ ስርዓቶች ህዝቦች በአብሮነትና በሰላም እንዲኖሩ የሚያደርጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

"በልዩነትታችን ውስጥ በአንድነት ተሳስሮ የመኖር እሴት ያለን ሲሆን ይህም ለሰው ልጅ ክብር በመስጠት የሚገለጽ ነው" ብለዋል።

በሀዋሳ ዩንቨርስቲ የስነሰብ ትምህርት ክፍል መምህርና የማህበረሰብ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዳኜ ሽብሩ በበኩላቸው መቻቻል ለአብሮነትና ለሰላም መሠረታዊ ነገር መሆኑን ተናግረዋል።

"በሉላዊነት ሰበብ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ ነው" ያሉት ዶክተር ዳኜ ዘመናዊነትን ስንከተል ማንነታችንን ማወቅና ወግ ባህላችንን በመጠበቅ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የተለያዩ ብሔረሰቦች ሰላም ለመፍጠርና ግጭት ለመፍታት የሚጠቀሟቸው ባህሎችን አውቀን በትምህርት ስርዓት ውስጥ በማስገባት ለልጆቻችን ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

"ሽምግልና እየተተወና እየቀረ ባህል እየተበረዘ መምጣቱ ለሰላም እጦት ትልቅ ድርሻ አበርክቷል" ያሉት ደግሞ የቡርጂ ሀገር ሽማግሌ አቶ ማምሩ ጎጅሬ ናቸው።

ባህልን መጠበቅ በመሳኑና ለሽማግሌዎች ክብር ባለመሰጠቱ ችግሩ መፈጠሩን ጠቁመው "ዛሬ ላይ ቀበሌ ከቀበሌ እየተጋጨ ህይወት ሲጠፋ" መመልከት የመሰለ አሳዛኝ ነገር የለም ብለዋል።

የደቡብ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አቡቶ አኒቶ በበኩላቸው ክልሉ የበርካታ ቱባ ባህል መገኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ግጭቶች ሲከሰቱ መፍታት የሚያስችለው የዕርቅ ስነ ሰርዓት በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመው ባህል ህብረተሰቡ በሰላም እንዲኖር ከማድረግ አንጻር ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ሀላፊው ገለጻ በክልሉ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ባህላዊ እሴቶች እንዳይበረዙ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም