የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ደርሷል - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ - ኢዜአ አማርኛ
የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ደርሷል - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ
አዲስ አበባ መጋቢት 14/2013 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ባንኮች ለግሉ ሴክተር የሚያቀርቡት ብድር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ነው ያነሱት።
በተለይ ከገንዘብ ለውጡ በኋላ ተጨማሪ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የባንክ ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት።
ይህም ተጨማሪ 100 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ባንኮች እንዲገባ ማድረጉን አብራርተዋል።
ባንኮች ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 255 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠታቸውን ጠቁመው፤ ከቀረበው አጠቃላይ ብድር 74 በመቶው ለግሉ ዘርፍ መሰጠቱን ተናግረዋል።
ለአብነትም በ2010 ዓ.ም የግሉ ዘርፍ ባንኮች ከሚያቀርቡት አጠቃላይ ብድር 45 በመቶ ብቻ ይጠቀሙ እንደነበረ ነው የጠቀሱት።
የግሉ ዘርፍ ከፍተኛውን የብድር ምጣኔ ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉ ደግሞ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የዋጋ ግሽበት ግን አሁንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ይህም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች እየጎዳ መሆኑን ገልጸው፤ የምርት እጥረቱ እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ነጋዴዎች የችግሩ ኣባባሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ችግሩን ለማቃለል የእርሻ ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ የተለያዩ ስልቶች ተቀይሰው እየተሰሩ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በማብራሪያቸው በግማሽ ዓመቱ የኤክስፖርት መጠንም 21 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አንስተዋል።
በዚህም ወርቅ ከሁሉም ዘርፎች በላይ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ መሆኑን ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል በአንበጣ መንጋ፣ በጎርፍ እና በፀጥታ ችግሮች በመፈጠራቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ሃብት መባከኑን ጠቅሰዋል።