ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ 21 በመቶ እድገት አሳይቷል...ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ 21 በመቶ እድገት አሳይቷል...ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
መጋቢት 14/2013(ኢዜአ) “ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ 21 በመቶ እድገት አሳይቷል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ።
በማብራሪያቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት፤ የወጪ ንግድ ውጤት ግምገማ 21 በመቶ እድገት አለው።
የተገኘው የወጪ ንግድ ውጤት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ተሻሻለ በተባለበት ባለፉት 20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በዚህ ስምንት ወር የመጣውን ያህል ውጤት በቁጥር ደረጃ አምጥቶ እንደማያውቅም ገልጸዋል።
ኮቪድ-19፣ አንበጣና ግጭት እያለ የወጪ ንግድ እድገትን ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።“በተለይ ወርቅን በሚመለከት ከሪፎርም በፊት አንዳንድ ወርቅ ማምረቻ የኢንቨስትመንት ቦታዎች የተዘጉና ስራቸውን ያቆሙ” ነበሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጉጂን በአብነት አንስተዋል።
ከኩባንያዎች ጋር በመነጋገር ስራ ያቆሙ የወርቅ ማምረቻ ኩባንያዎች ስራ እንዲጀምሩ በማድረግ፣ አዳዲስ ኩባንያዎችን በማስገባት የወርቅ ምርትና ወጪ ንግድ በብዙ እጥፍ እንዲያድግ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በሚቀጥሉት ወራት አዳዲስ የገቡ ፋብሪካዎች ወደ ምርት ስለሚገቡም መጠኑ እያደገ እንደሚሄድ ገልጸው፤ “በተወሰነ ደረጃ ዓለም ላይ ካለው ጫና ጋር ተያይዞ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የውጭ ምንዛሬ መጠን ቀንሷል” ብለዋል።
መታየት ያለበት ባሉት ፈተናዎች ውስጥ በመሆን የወጪ ንግድ አድጓል የሚለው መሆኑን ጠቅሰው፤ 21 በመቶ እድገት ማረጋገጥ ቀላል ውጤት እንዳልሆነ አመልክተዋል።
በ2010 ዓ.ም የነበረው የንግድ ሚዛን ከዜሮ በታች ነጌቲቭ 14 ነጥብ 7 እንደነበር አስታውሰው፤ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የ4 ነጥብ 6 መሻሻል ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።
ውጤቱ የመጣው በወጪ ንግድ ማደግ ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው፤ በገቢ ሸቀጦች ላይ በሚደረግ ቁጥጥር ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህንን በሚቀጥሉት አመታት ማስቀጠል ከተቻለ የንግድ ሚዛን መዛባቱ እየቀነሰና እየተስተካከለ እንደሚመጣ ጠቁመዋል።