በጎንደር ከተማ ቱርክ ሰራሽ የሆኑ 599 ሽጉጦችን ደብቀው የተገኙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ ቱርክ ሰራሽ የሆኑ 599 ሽጉጦችን ደብቀው የተገኙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

መጋቢት 13/2013(ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ቱርክ ሰራሽ የሆኑ 599 ሽጉጦችን በተሽከትካሪ ውስጥ ደብቀው የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ።
የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒክሽን ሃላፊ ዋና ኢንስፕክተር እየሩስ አስማረ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሰር የዋሉት ዛሬ ረፋድ አምስት ሠዓት አካባቢው በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ነው።
ግለሰቦቹ በከተማው ወለቃ በተባለው የፍተሻ ኬላ ሽጉጦቹን በተሽከርካሪ አካል ውስጥ ደብቀው ለማሳለፍ ሲሞክሩ እንደተደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡
የጸጥታ ሃይሉ ባደረጉት ጥብቅ ፍተሻ ሽጉጦቹን የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 - 62511 አዲስ አበባ በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ አካል ውስጥ በረቀቀ መንገድ በመበየድ ለመመሸግ ቢሞከርም በተደረገ ፍተሻ ማግኘት መቻሉን አሰታውቀዋል፡፡
ተሽከርካሪው መነሻውን ሳንጃ ከተማ በማድረግ ወደ ጎንደር ከተማ ለመግባት ሙከራ ማድረጉን የጠቆሙት ዋና ኢንስፔክተሯ የጦር መሳሪያው ከሱዳን የመጣ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ሾፎሩና በተሽከርካሪው ተሳፍሮ የነበረ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያናጋ በመሆኑ ህብረተሰቡ ለፖሊስ እያደረገ ያለውን ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡