በሀዋሳ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነናል ...ነዋሪዎች

16

ሀዋሳ ፤ መጋቢት 13/2013 (ኢዜአ)፡- በዘንድሮ የበጋ ወቅት ወጣቶች ባከናወኗቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ወጣቶቹ እስካሁን በሀዋሳ ከተማ  እስከ 12 ሚሊዮን ብር  የሚገመቱ ስራዎች ማከናወናቸው ተመልክቷል።

በሀዋሳ ምስራቅ ክፍለ ከተማ በጎዳና ይኖሩ የነበሩት አቶ አደም ደዩ በሰጡት አስተያየት፤ ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ሀገራቸውን ከጠላት ለመታደግ ተሳትፈው በካራማራ በተገኘው ድል አስተዋጽኦ እንደነበራቸው አውስተዋል።

ረዳት የሌላቸው በመሆኑ ምክንያት ለጎዳና ኑሮ ተዳርገው እንደቆዩ የአካባቢው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ቤት ሰርተው መጠለያ አመቻችተውላቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሃዋሳ  የቀድሞ መናኸሪያ ጀርባ የቆሻሻ መጣያና የወንጀል ድርጊቶች ይፈጸምበት የነበረውን ቦታ  በጎ ፈቃደኞች አጽድተው በማስዋብ በአካባቢው በንግድ ስራ እንዲሰማሩ እንዳስቻሏቸው የተናገሩት ደግሞ  ወይዘሮ ርብቃ ሁሴን ናቸው፡፡

ወጣቶቹ ይህን ስፍራ በበጎ ፈቃደኝነት ባይመቻችላቸው የሚተዳደሩበት ስራ አጥተው ይቸገሩ እንደነበር ገልጸው ወጣቶች ለሚያከናውኑት የበጉ አድራጎት ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

 ወጣት ቤተልሄም ተስፋዬ  በበኩሏ በዚሁ ስፍራ የሻይ ቡና ሥራ እየሠራች እንደምትገኝና ከዚህ ቀደም በሴተኛ አዳሪነት አስከፊ ህይወት ማሳለፏን ተናግራለች።

 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ  በዚህ ቦታ ላይ ሰርታ ራሷን ለመቀየር የሚያግዛት ድጋፍ  ማድረጋቸውን ገልጻለች።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር በከተማዋ ባለፉት ወራት 23 የአረጋዊያን ቤቶች መጠገናቸውን፣ 28 የቆሻሻ መጣያና ለእንቅስቃሴ አስፈሪ የነበሩ ስፍራዎች አጽድተው ለብዙዎች የስራ ዕድል መፍጠሪያ ስፍራ ማድረጋቸውን የገለጸው ደግሞ በጎ ፈቃደኛ ወጣት  አወቀ አራርሶ ነው።

ከዚህም ባለፈ በአካባቢው ሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሷል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ወጣቶች ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሲሩ ሁንጋታ በበኩላቸው በደም ልገሳ፣ ከተማ ውበት፣ ማዕድ ማጋራት፣አረንጓዴ ልማትና መሰል የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ  ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም እስካሁን  እስከ 12 ሚሊዮን ብር  የሚገመቱ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አክሊሉ ዓለሙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት በደም ልገሳ፣ የአረጋዊያን ቤት በመጠገን፣ ሠላምና ጸጥታን በማስጠበቅ ፣ ከተማን በማስዋብና በሌሎችም የስራ ዘርፎች ላይ እየተሳተፉ  መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ከ320 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመሳተፍ እስካሁን ያከናወናቸው ስራዎች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም