የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ በአዋሽ 7 ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን 11ኛ ዙር የጀማሪ አመራሮችንና 15ኛ ዙር የረጂም ርቀት ሬዲዮ ኦፕሬተሮችን አስመረቀ

182

መጋቢት 13 /2013 (ኢዜአ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ለተከታታይ ለ2 ወራት በአዋሽ 7 ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን ከ4 መቶ በላይ 11ኛ ዙር የጀማሪ አመራሮችና 15ኛ ዙር የረጂም ርቀት የሬዲዮ ኦፕሬተሮችን በትላንትናው እለት ማስመረቁ ተገለጸ፡፡

ጀማሪ አመራሮቹ በስልጠና ቆይታቸው ህገ-መንግስት፣ የወንጀል ህግና የወንጀል ስነ-ስርዓት ህግ፣ ፌደራሊዝም፣የስራ አመራር ኮርስ፣ ፖሊሳዊ ዲስፕሊን፣መልካም አስተዳደር፣የቅድመ ወንጀል መከላከልና የፖሊስ ዶክትሪንን ጨምሮ ሌሎች መሰል ትምህርቶችን ለ212 ሰዓታት መውሰዳቸው ተገልጿል፡፡

የረጂም ርቀት የሬዲዮ ኦፕሬተሮችም መሰረታዊ የረጂምና የአጭር ርቀት ሬዲዮ ግንኙነት ማኑዋሎች፣ የኦፕሬተር ተግባርና ኃላፍነት፣ የመረጃ አያያዝና ሚስጥራዊ ሰነዶች፣ የሳይፈር ኮድ እና የኮፒውተር ትምህርቶችን ለ323 ሰዓታት መከታተላቸው ተነግሯል፡፡

በተመሳሳይ ተመራቂዎቹ የአካል ብቃትና ወታደራዊ ስልጠናዎችን ለ147 ሰዓታት መሰልጠናቸው ታውቋል፡፡

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲካሄድና ፖሊስ ከየትኛውም የፖለትካ ወገንተኝነት ገለልተኛ ሆኖ የህግ ማስከበር ስራ እንዲሰራ ተቋሙ የፖሊስ ዶክትሪን በመቅረፅ በየደረጃ ላሉት የፖሊስ አመራሮችና አባላት ስልጠና እየሰጠ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ የሰው ሀብት ስራ አመራር ስልጠና ምክትል ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ሰማኝ ይደነቅ ተናግረዋል፡፡

የፖሊስ አመራሮችንና አባላትን አቅም ለማጠናከር የጀመሩትን ስልጠና ለማስቀጠል በቅርቡ የአድማ ብተና አመራሮችን በሁለት ዙር ለማሰልጠን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ፅህፈት ቤትና ስታፍ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር እሸቱ ፊጣ ለተመራቂዎቹ የስራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት ተመራቂዎቹ ከስልጠና ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥና የህዝብ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ ሀገራችንን በጀግንነት መጠበቅ፣ህዝባችንን በሰብዓዊነትና በቅንነት ማገልገል አለባችሁ ሲሉ መሳሰባቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም