የጨረራና ኒዩኩሌር ቴክኖሎጂን ለማጎልበት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ጨረራ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የጨረራና ኒዩኩሌር ቴክኖሎጂን ለማጎልበት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ጨረራ ባለስልጣን
መጋቢት 13/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ፈርጀ ብዙ ችግሮችን የሚፈታውን የጨረራና ኒዩኩሌር ቴክኖሎጂ ለማጎልበት እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ጨረራ ባለስልጣን አስታወቀ።
የጨረራና ኒዩኩሌር ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ ጥቅም በሚውሉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ ነው።
የዓለም ሀገራት አሁን ለደረሱበት እድገት ቴክኖሎጂውን እንደ ዋነኛ አማራጭ እየተጠቀሙበትም ነው።
ኢትዮጵያም ከዘርፉ የሚገባትን አገልግሎት ለማግኘት በማለም ነው ባለስልጣኑን በአዋጅ በማቋቋም ወደ ትግበራ የገባችው።
የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው በተለይም ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ቴክኖሎጂው በጤናው ዘርፍ ከምርመራ ጀምሮ የተሟላ ህክምናን እስከ መስጠት የማይተካ ሚና አለው።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የማምረትና ሙሌት ልኬት፣ በመንገድ ስራ የኮንክሪት ጥቅጣቆ መጠን ልኬት እንዲሁም ለማዕድን እና ውሃ ዳሰሳ የሚያገለግል ቴክኖሎጂ መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ ሰለሞን አክለውም ቴክኖሎጂው በተለይም በግብርናው ዘርፍ ለገንዲ በሽታ ምክንያት የሆነውን የቆላ ዝንብ ለማምከንና ለምርጥ ዘር ብዜት ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂው ኢነርጂ በማመንጨት የሚሰጠው ጥቅም ደግሞ አሁን አሁን ወደ ማይተካ የዓለም ሀገራት አማራጭ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የጨረራና ኒዩኩሌር ቴክኖሎጂ ከሚሰጠው ግልጋሎት ባልተናነሰ መልኩ ጥንቃቄ ከጎደለው ጉዳቱ የከፋ መሆኑንም ተናግረዋል።
የጨረራ ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ ፍቃድ ከመስጠት አንስቶ በአገልግሎቱ የጥንቃቄ ሂደቱን የመቆጣጠርና አገልግሎቱን ባጠናቀቁ ጊዜ አወጋገዱ ድረስ የመቆጣጠር ስራ ደግሞ ለባለስልጠኑ በአዋጅ የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገሪቷ ከቴክኖሎጂው የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ዘርፉን የሚመራ የሰው ሃይል ግንባታና ማህበረሰቡ ለቴክኖሎጂው ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በተለይም በጨረራና ኒዩኩሌር ቴክኖሎጂ ለዘርፍ የሰው ሃይል ግንባታና ምርምር ተቋም ግንባታ ለማካሄድ ከዓለም ሀገራት የላቀ ልምድና ተሞክሮ ካላት የሩሲያ ጋር ስምምነት መፈራረሟን ተናግረዋል።
በሀገራቱ መካከል የተደረገው ስምምነትም ሀገሪቷ ለቀጣይ 20 እና 30 ዓመታት በዘርፉ ሊትደርስ ላሰበችው ግብ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል።