ቀጥታ፡

የወሎን የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴት ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው

ደሴ፤ መጋቢት 13/2013(ኢዜአ) የወሎን የአብሮነት፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እሴት ለትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን 15ኛው የባህል ፌስቲቫልና ቲያትር ውድድር በደሴ ከተማ ተካሄዷል፡፡

ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ የመምሪያው  ኃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ እንደተናገሩት፤ ባህል በአንድ አካባቢ የሚኖር ማህበረሰብ የጋራ መገለጫ በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ መተላለፍ አለበት።

የወሎ ህዝብም ሃይማኖት፣ ብሄርና ሌሎች ጉዳዮች ሳይለዩት በአብሮነት፣ ፍቅርና ሰላም ተከባብሮ በመኖር ከሀገር  አልፎ ለዓለም ምሳሌ ሊሆን የሚችል እሴትና ጸጋ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሯሯጡ ፖለቲከኞች ለዘመናት የዘለቀውን የወሎ ህዝብ እሴትና ጸጋ በእኩይ ሴራቸው በመበረዝ አካባቢውን የብጥብጥ ቀጠና ለማድረግ በተደጋጋሚ ሲሰሩ ይስተዋላል ብለዋል፡፡

መምሪያው ይህን መሰረታዊ ችግር በመፍታት የወሎን የጥንት ባህልና እሴት በማስተማር ለትውልዱ ለማስተላለፍ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ለዚህም የሐይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች በየእምነት ተቋሙ፣ በየእድሩ፣ በየሰፈሩና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ   ህብረተሰቡን  በተለይም ወጣቱን በማስተማር ባህልና ወጉን እንዲጠብቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እየተስተዋለ ያለው ግድያ፣ መፈናቀል፣ ሁከትና ብጥብጥ ከኢትዮጵያ ባህልና እሴት ያፈነገጠ በመሆኑ ሁሉም ማውገዝ አለበት ያሉት ኃላፊው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጥበባትና ቲያትር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ መኳንት ሙላቴ በበኩላቸው የወሎን ባህልና እሴት ለትውልድ ለማስተላለፈት ኪነ ጥበብ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲውም ትውልዱ ባህልና እሴቱን ጠብቆ የኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም እንዲረጋገጥ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጀት በመስራት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የባህል ቡድን አስተባባሪ አቶ ዘካሪያስ በላይ ቡድናቸው በድንገት በሚፈጠር ግድያ ምክንያት ደም ለመመለስ በሚል የሚፈጠረውን ችግር የሚያሳይ "አውፉታ" የሚል ቴአተር ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

የቲያትሩ ዋና ጭብጥም በደም መመላለስ የሚፈጠረውን የተወሳሰበውን ችግር ለማስቆም በ"አበጋሮች" እና በሃገር ሽማግሌዎች ጥረት እርቀ ሰላም እንዲወርድ የሚሄዱበትን መንገድና ውጤቱን የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል።

አንዴ የሞተ ሰው ላይመለስ የሌሎች ንጹሃን ዜጎች ህይወት መጥፋት የለበትም፤  የአባቶቻችን ባህልና እሴት ብንጠብቅ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች አይፈጠሩም ነበር ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የባህል ፌስቲቫልና ቲያትር ውድድር በዞኑ ያሉ ወረዳዎች የተሳተፉ ሲሆን ቃሉ፣ ኮምቦልቻ እና ተሁለደሬ ወረዳዎች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡

የቃሉ ወረዳ የባህል ቡድን "የሲኦል ሰልፈኞች" በሚል ያቀረበው ቲያትር በክልል ደረጃ ከመጋቢት 26 እስከ ሚያዚያ 3/2013ዓ.ም. በባህርዳር ከተማ በሚካሄደው የባህል ፌስቲቫልና ቲያትር ውድድር ላይ  ዞኑን እንዲወክል ተመርጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም