ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩና መረጃውን ተቀብለው የሚያናፈውሱ አካላት ከህገ-ወጥ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩና መረጃውን ተቀብለው የሚያናፈውሱ አካላት ከህገ-ወጥ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ
መጋቢት 13/2013(ኢዜአ) ከተገቢው አካል መረጃ ሳይጠይቁና ሳያረጋግጡ ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩና መረጃን ተቀብለው የሚያናፈውሱ አካላት ከህገ-ወጥ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ።
ከተማዋ ላይ ሰላም እንደሌለ በማስመሰል ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ላይ ክትትል በማድረግ ምርመራ በማጣራት በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች የህብረተሰቡን በጋራ አብሮ የመኖር እሴቶችን የሚያናጉ ሀሰተኛ መረጃዎች እየተሠራጨ ነው።
የሀገሪቱ ሠላም እንቅልፍ የሚነሳቸው ፀረ ሠላም ሀይሎች ብሄርን ከብሄር ለመጋጨት በአዲስ አበባ ብሄርን እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሊፈፀም ነው የሚል ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጩ መሆኑንም አስታውቋል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተላለፈው ሃሰተኛ መረጃ የአዲስ አበባ ፖሊስን የደንብ ልብስ የለበሱ ነገር ግን የፖሊስ መታወቂያ የሌላቸው ጸጉረ ልውጥ ወጣቶች በየቤቱ እየዞሩ ብሔር እና ሃይማኖት በመመዝገብ ላይ ናቸው የሚል መውጣቱንም መግለጫው አመልክታል።
እነዚህ ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ጸጉረ ልውጦች በተወሰኑ ብሔሮችን እና ሃይማኖቶችን ለይተው ለማጥቃት እየተንቀሰቀሱ ነው የሚሉ እና በነዋሪው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ሃሰተኛ መረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ መሆኑንም ኮሚሽኑ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
በፀረ ሠላም ሀይሎች አየተሠራጨ ያለው ሀሰተኛ መረጃ ህብረተሰብን ለማደናገጥ እና ለማሸበር፤ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት እንዲሁም በህብረተሰቡ ላይ የፀጥታ ስጋት ለመፍጠር ሆን ተብሎ ታቅዶና ታስቦ እየተሰራጨ ያለ ሀሰተኛ መረጃ መሆኑም ተገልጿል።
በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ሀሰተኛ መረጃ በስፋት የተሰራጨ በመሆኑ በሰዎች የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ የስነ ልቦና ጫና እያሳደረ ነው ብሏል የኮሚሽኑ መግለጫ።
ከተገቢው አካል መረጃ ሳይጠይቁና ሳያረጋግጡ ሀሰተኛ መረጃ የሚሰራጩ እንዲሁም መረጃን ተቀብለው የሚያናፈውሱ አካላት ከህገ-ወጥ ተግባራቸው እንዲቆጠቡም ኮሚሽኑ እያሳሰበ፤ ከተማዋ ላይ ሰላም እንደሌለ በማስመሰል ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ላይ ክትትል በማድረግ ምርመራ በማጣራት በህግ እንዲጠየቁ እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት መደበኛ ተግባራቸውን በአግባቡ እየተወጡ እንደሚገኙ እና ነዋሪውም የእለት ተእለት ተግባሩን እያከናወነ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልፆል፡፡
ህብረተሰቡ በፀረ- ሰላም ኃይሎች የሚናፈሱ መረጃዎች ፍፁም ሀሰተኛ መሆኑን በመረዳት ከፀጥታ አካላት ጋር ያለውን ትስስር አጠናክሮ እንዲቀጥል እና የከተማዋን ፀጥታ አስመልክቶ የሚተላለፉ መረጃዎችን ከተገቢው አካል የሚለቀቁትን ሊከታተል እንደሚገባም አስታውቋል፡፡
ህብረተሰቡ ለጸጥታ ስራ እያበረከተ የለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትና አጠራጣሪ ጉዳይ ሲያጋጥም ጥቆማ ለመስጠት ነፃ የስልክ መስመር 991ወይም 01-11-11-01-11መጠቀም እንደሚቻል የአዲስ አበባ ፖሊስ መልእክት አስተላልፏል ።