ቀጥታ፡

የህግ ማስከበር ዘመቻውን በስኬት ለመሩ የመከላከያ ጀነራሎች የአፋር ህዝብ ከፍተኛ የጦር ሜዳ ኒሻን ሸለመ

ሰመራ፣ መጋቢት 13/ 2013 (ኢዜአ) የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሀገር ክህደት ወንጀል በፈጸመው የጁንታ ቡድን ላይ የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በስኬት ለመሩ የመከላከያ ጀነራሎች የአፋር ህዝብ ከፍተኛ የጦር ሜዳ ኒሻን ሸለመ።

የጦር ጀነራሎቹ ከክልሉ መንግስትና ህዝብ የተሸለሙት በአፋር ህዝብ ብስለት በተሞላበት የአመራር ጥበባቸው፣ በጀግንነታቸው፣ በአርቆ አሳቢነታቸውና በችግር ፈችነታቸው ከፍተኛ ብቃት የነበራቸው ጀግኖችና ባለታሪኮች የሚሰጠውን "መላሳይ " የተሰኘ የጦር ማዕረግ ስያሜ የያዘ የክብር ኒሻን ነው።

ከፍተኛ የጦር ሜዳ የክብር ኒሻኑ የተበረከተላቸው የኢፌደሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ዋና ኢታማጆር ሹም ጂነራል ብርሀኑ ጁላ፣ ለምክትል  ኢታማጆር ሹም ሌተናል ጀነራል አበባው ታደሰና ለሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ነው።

የአፋር ክልል ርእሰ መሰተዳደር አቶ አወል አርባ ለጦር ጀነራሎቹ የአፋር ህዝብ ከፍተኛ የጦር ሜዳ ኒሻን በሽልማት አበርክተዋል።

ለጦር ጀነራሎቹ በሰመራ ከተማ የቤት መስሪያ ቦታም በሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በእውቅናና ምስጋና ስነ-ስርአቱ ላይ እንደገለጹት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለዘመናት የሀገር ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች በመሳተፍ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ሆኗል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ሀገራዊ ግዳጁን በብቃት ከመፈጸም በተጨማሪ የትግራይን ህዝብና ደህንነት በመጠበቅ እንዲሁም ህብረተሰቡን በተለያዩ የልማት ስራዎች በመደገፍ ወገናዊ አጋርነቱን ያስመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል።

"የህዋሃት ጁንታ ቡድን የነበረውን ከፍተኛ የስልጣን ጥም በአቋራጭ ለማሳካት በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የመፈጸሙ ድንገተኛና አስነዋሪ ጥቃት ታሪክ ይቅር የማይለው ግልጽ የሃገር ክህደት ተግባር ነው" ብለዋል።

"በተለይም ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ተናበው ሀገር ለመበተን  በሚንቀሳቀሱበት  አስቸጋሪ ሰዓት የተፈጸመው ጥቃት ሁሌም ትውልድ ሲያወግዘው የሚኖር ጥቁር ታሪክ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

ጥቃቱን ተከትሎ የሀገር ደህንነትን ለማረጋገጥ በጁንታው ላይ የተካሄደ የህግ ማስከበር ዘመቻን የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሁለት ሳምንት አጠናቆ  አኩሪ ገድል መፈጸሙን አመልክተዋል።

ሰራዊቱ አስነዋሪ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወንጀለኞችን አድኖ ለህግ በማቅረብም ስኬታማ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ርእሰ መስተዳደሩ፤ የቀሩ ጁንዎችንና ተላላኪዎቻቸውን በመለቃቀም ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ የህግ ማስከበር ተግባሩን ለመሩና ከፍተኛ አስተዋጾ ላደረጉ የጦር ጀነራሎች  ያዘጋጀውን የክብር ኒሻን በማስረከባቸው ከፍተኛ ክብርና ኩራት እንደሚሰማቸው ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

የኢፌደሪ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ዋና ኢታማዥር ሹም ጂነራል ብርሀኑ ጁላ በበኩላቸው የአፋር ህዝብና መንግስት፣ እንዲሁም  ልዩ ሀይልና ሚኒሻ ከወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን በህግ ማስከበሩ ተግባር የአፋር የቆየ ሀገር ወዳድነት ባህሉን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

"አፋርን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክ ለከሀዲና ለወራሪ እጅ የማይሰጥና ጀግና ህዝብ ነው" ብለዋል።

ጂነራል ብርሀኑ ጁላ ለተደረገላቸው እውቅናና ሽልማት በሀገር መከላከያ ስም ለአፋር መንግስትና ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በተካሂደው የእውቅናና ሽልማት ስነ ስርአት ላይ  በህግ ማስከበር ተግባር መስዋእት ለሆኑ የህሊና ጸሎት ተደርጓል።

የጦር ጀነራሎቹ ትናንት ሰመራ ሱልጣን አሊሜራህ አየር ማረፊያ በደረሱበት ወቅትም  የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባና ከፍተኛ አመራሮች አንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም