ቀጥታ፡

በስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረኩ ነው- ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ

ሀረር መጋቢት 13/2013 ( ኢዜአ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በኩታ ገጠም ተደራጅተው በስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን -የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በዞኑ በጉርሱም ወረዳ በስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ማሳ ተጎብኝቷል።

የዩኒቨርሲቲው መምህር፣ ተመራማሪና የዘር ቁጥጥር ማረጋገጫ ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አብዲ መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን አርሶ አደር የምርት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

በጉርሱም ወረዳ የሃሮ ባቲ ቀበሌ አየር ንብረትና አፈር በማጥናት ምቹና ምርታማ የሚያደርጉ የሰብል አይነቶችን በማቅረብ፣ የባለሙያ ክትትልና ድጋፍ የማድረግና በሌሎች የግብርና ግብዓቶች አቅርቦት እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በቀበሌው በበጋው ወቅት በኩታ ገጠም ተደራጅተው በ60 ሄክታር ማሳ ላይ በመስኖ የታገዘ የስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት እያካሄዱ ላሉ አርሶ አደሮች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።

እንደ ሀገር በሰንዴ እራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ስኬታማ ማድረግ እንደሚገባም ዶክተር አብዲ አስታውቀዋል ።

የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ግብርናና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጌታሁን ንጋቱ በበኩላቸው  በአርሶ አደሮቹ ማሳ ላይ እየተባዛ ካለው የስንዴ ምርጥ ዘር 2ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

በዞኑ በበጋው ወቅት በመስኖ በመታገዝ አጠቃላይ በ6 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየተካሄደ ካለው የስንዴ ልማት 340 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅምአስታውቀዋል ።

"ቀደም ሲል የክረምት ወቅትን እየጠበኩ ድንች ብቻ ሳመርት ቆይቻለሁ" ያሉት ደግሞ በጉርሱም ወረዳ የሀሮ ባቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ያህያ ዩሱፍ ናቸው ፡፡

ዘንድሮ ከዞኑ ግብርናና ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ በመታገዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ የስንዴ ምርጥ ዘር እያባዙ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በማሳ ላይ ባለው የሰብሉ ይዘት አኳያ በልማቱ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተስፋ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ቀደም ሲል በአመት አንድ ጊዜ በቆሎ ብቻ ሲያመርቱ እንደቆዩና ምርታማነታቸውም ዝቅተኛ እንደነበረ የገለፁት ደግሞ አርሶ አደር ነጅሃ አብዲ ናቸው፡፡

ዘንድሮ መሳተፍ በጀመሩበት የስንዴ ልማት ስጋት ገብቷቸው እንደነበር የገለጹት አርሶ አደሯ ልማቱን ከጀመሩ በኋላ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ስራ ጎን ለጎን በአዝዕርት፣በእንሰሳት ሃብት ልማት፣በጤናና በሌሎች 229 ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች እያከናወነ መሆኑ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም