ቀጥታ፡

ፖሊሲና መሪ እቅዱ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል -የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች

ጎባ፣ መጋቢት 12/2013 (ኢዜአ) በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተዘጋጀ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፖሊሲና መሪ እቅድ በአግባቡ ከተተገበረ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ችግሮችን መፍታት ያስችላል ሲሉ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ተናገሩ።

ዩኒቨርሲቲው አመራሮች በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም በተቋሙ የ10 ዓመት መሪ እቅድ ዙሪያ ያካሄዱትን የስልጠናና የምክክር መድረክ ትላንት አጠናቀዋል።


የዩኒቨርሲቲው መምህር መለሰ ጫላ እንደገለጹት ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም የነበረው የትምህር ፖሊሲና መሪ ዕቅድ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል በማጥናት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ አሉታዊ ተጽእኖ ሲያሳድር ቆይቷል፡፡


አሁን ለትግበራ የተዘጋጀው የትምህርት ፖሊሲና ስትራቴጂ ዩኒቨርሲቲዎችን በተለያዩ የትኩረት መስኮች በመከፋፈል ገበያን ያማከለ የሰው ኃብት ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

“ያለፍንበት የትምህርት ሥርዓት በዕውቀት ፣ ክህሎትና ሥነምግባር ብቁ ያልሆኑ ምሩቃንን በተግባር ያየንበት ነው” ያሉት ደግሞ ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ ዶክተር መሐመድ ጀማል ናቸው፡፡ 


ዶክተር መሐመድ እንዳሉት እየተቀረፀ ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ በፊት የነበሩ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ የአሰራር ስልቶችን ይዞ የቀረበ መሆኑን ከስልጠና ሰነዱ መረዳታቸውን ገልጾዋል፡፡ 

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተዘጋጁ የሚገኙ አጠቃላይ የትምህርት ፖሊሲ ሰነድ ለሀገር በቀል እውቀቶች እውቅና የሚሰጡና ለትምህርት ጥራትና አግባብነት ችግሮች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን ነቅሶ ያቀረበ ነው” ያሉት ደግሞ ዶክተር ቢፍቱ ገዳ ናቸው፡፡ 

የተነደፉት ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን ወደ ተግባር በመቀየር የትምህርት ጥራት አግባብነት ችግሮችን መቅረፍ ይቻለል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል መድረኩ በትምህርት ዘርፉ ለሚቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ለአመራሩ ግንዛቤ ለመፍጠርና ግብዓት ለማሰባሰብ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“እስካሁን ስንመራበት የቆየነው የትምህርት ሥርዓታችን በርካታ መቀረፍ የሚገባቸው ችግሮች አሉበት” ያሉት ዶክተር አህመድ በተለይ የትምህርት ጥራት ፣ አግባብነትና ፍትሀዊነት ላይ ሰፊ ጉድለቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በሀገር ደረጃ እየተቀረፁ ያሉት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ችግሮቹን ነቅሶ በማውጣት የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀመጡ መሆናቸውን አመልክተው ዩኒቨርሲቲው መሪ ዕቅድም ከሀገር አቀፉ ጋር አስተሳስሮ መቃኘቱን አስረድተዋል።

ዶክተር አህመድ እንዳሉት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ከሰለጠኑባቸው ሰነዶች መካከል የሰው ሃብት ልማት፣ ሳይንሳዊ ምርምርና ፈጠራ፣ የኢንተርፕራይዝ ልማት፣ መሰረተ ልማትና ግብዓት የሚሉት ይገኙበታ፡፡

ለሁለት ቀን በተዘጋጀው የስልጠናና የምክክር መድረክ ላይ ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ኮሌጆች የተውጣጡ አመራሮች ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም