ቀጥታ፡

“ፀረ ኢትዮጵያና ሀገር አፍራሽ የሆኑ ኃይሎች በንጹሃን ላይ እየፈፀሙ ያሉትን ጥቃት ለማስቆምና ለመቆጣጠር ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው”...የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

መጋቢት 12/ 2013 (ኢዜአ) ፀረ ኢትዮጵያና አገር አፍራሽ የሆኑ ኃይሎች በንጹሃን ላይ እየፈፀሙ ያሉትን ጥቃት ለማስቆምና ለመቆጣጠር ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ተጨማሪ የፀጥታ አካላትን ወደ ሥፍራው በማሰማራት ጥቃቱን ለመቆጣጠርና ንጹሐን ዜጎችን ለመታደግ እየሠራ እንደሚገኝ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታውቀ።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫው የክልሉ መንግስት የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቆ “ህዝባችን በሰላም ተረጋግቶ የሚኖርበትና ሰላማዊ የሆኑ ዜጎች ሁሉ በነጻነት ተንቀሳቅሰው የሚሰሩበት ሰላማዊ ክልል እንዲሆን አድርጓል” ብሏል፡፡

“በህዝቡ ፣ በአመራሩና በጸጥታ መዋቅሩ ጥምረት የትህነግ ቅሪቶች እንዲሁም የትህነግ ተላላኪ የሆኑ ኦነግ ሸኔና መሰሎቹ በየቦታው የሚፈጥሩትን ትንኮሳዎች ሁሉ በአስተውሎትና በሰከነ የትግል ሥልት እያሸነፍን ህዝባችን የሰላም አየር እየተነፈሰ ከድህነት ለመውጣትና ኑሮውን ለማሻሻል መደበኛ ህይወቱ ላይ አተኩሮ የሚሰራበት ጊዜ ላይ ደርሰናል” ሲልም መግለጫው አመልክቷል።

“የአሁኑ ግጭት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢዎች የተፈጠረ ሲሆን ሐሙስ መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ጅሌ ጥሙጋ ላይ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጠብ ምክንያት አንድ ሰው ህይወት ህልፈትን ምክንያት በማድረግ የተቀሰቀሰ ነው፡፡

“በግለሰቦች መካከል የነበረውን ግጭትና የደረሰውን ሞት ምክንያት በማድረግም በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቅ መፈጸሙን ያስታወሰው መግለጨው “ይሁን እንጂ የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ የሆኑ አካላት በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቀ ሰላም ወርዶ መፍትሔ ያገኘውን ክስተት ምክንያት በማድረግ ከዓርብ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም. ጀምሮ አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድና የቡድን መሣሪያ ጭምር በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ያለው የታጠቀ ኃይል በአጎራባቹ የሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማና አካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነውረኛ የሆነ ጥቃት ተፈጽሟል” ብሏል።

“የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሚያ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ህዝቦች ለዘመናት በሰላም የኖሩና እየኖሩ ያሉ መሆኑ እየታወቀ ሀገር በሰላም ውላ እንዳታድር የሚፈልጉት አንዳንድ ተላላኪዎች በንጹሐን ላይ የፈፀሙት ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው” በማለትም አመልክቷል።

በዚህ ጥቃት እጅግ የዜጎች ህይወት ማለፉን ንብረት መውደሙን የገለጸው መግለጫው ለጠፋው ህይወትና ለደረሰው የንብረት ውድመትም የክልሉ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እንደሚገልጽ አስታውቋል።

ይህ ጥቃት የተፈጸመው የክልላችን የፀጥታ መዋቅር ህግ በማስከበር የህልውና ዘመቻው ላይ ትኩረት እድርጎ እየተንቀሳቀሰ በሚገኝበት ወቅት ላይ መሆኑን አመልክቶ “ይህን ምክንያት በማድረግ በአጣየና አካባቢው ፀረ ኢትዮጵያ እና ሀገር አፍራሽ የሆኑ ኃይሎች ከዚህም ከዚያም ተቀናጅተው የክልላችን ህዝብ እረፍት ለመንሳትና ሀገር ለማተራመስ እያደረጉት ያለ አስነዋሪ ድርጊት መሆኑን የክልሉ መንግሥት በሚገባ ይገነዘባል” ብሏል፡፡

በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ይህ ወንጀለኛ ቡድን በንጹሃን ላይ እየፈፀመ ያለውን ጥቃት ለማስቆም ጥቃቱ ከጀመረበት ሰዓት ጀምሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ተጨማሪ የፀጥታ አካላትን ወደ ሥፍራው በማሰማራት ጥቃቱን ለመቆጣጠርና ንጹሐን ዜጎችን ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ እየሠራ ይገኛል እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በአጣየና በአካባቢው የተፈጸመውን ዝርዝር ጥቃት፣ የደረሰውን ሰብአዊና የንብረት ጉዳት መንግሥት በፍጥነት መረጃውን አጣርቶ ለህዝቡ ይፋ የሚያደርግ መሆኑንም አመልክቷል።

“አጥፊ የወንጀለኞችን ቡድንና በድርጊቱ የተሳተፉት ተባባሪ አካላትን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል ለህግ የሚያቀርብ መሆኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን” ብሏል መግለጨው፡፡

“ይህ ጥቃት በተፈጸመበት አካባቢም ሆነ በሌሎች የክልላችን አካባቢዎች የትህነግ ርዝራዦችም ሆኑ የትህነግ ቅሪት ተልእኮ አስፈጻሚና ፈጻሚ የሆኑ ኃይሎች የፈጸሙትንና የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመመከት ህዝባችን ከመንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል” ሲልም አክሏል፡፡

እነዚህ ኃይሎች እድሉን ካገኙ ኢትዮጵያን ለማፍረስም ሆነ ለማተራመስ በክልላችንና ከክልላችን ውጭ በሚኖረው ህዝባችን ላይ አሰቃቂ ጥቃቶችን ለመፈጸም እንደማያመነቱ ደጋግመን ተመለክተናል ያለው መግለጫው አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች የተፈጠረውን ግጭት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በክልላችን ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ግጭቱን ለማባባስ ጥረት የሚያደርጉ አከላታት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የክልሉ መንግሥት በጥብቅ ያሳስባል።

ህብረተሰቡ በየትኛውም አካባቢ ለፀጥታው ስጋት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥመው ለሚመለከተው የመንግሥት አመራርና የፀጥታ መዋቅር መረጃ በመስጠት እንዲተባበር የክልሉ መንግስት ጥሪ እንደሚያስተላልፍ ከአማራ ኮምንኬሽን ቢሮ የተጘኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም