በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ኢትዮጵያን ከመበተን ታድጓል - በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ኢትዮጵያን ከመበተን ታድጓል - በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን
መጋቢት 12/2013 (ኢዜአ) “በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ኢትዮጵያን ከመበተን ታድጓል” ሲሉ በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ።
በሱዳን ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን "ለሀገራችን ሉዓላዊነትና አንድነት ከመንግስታችን ጎን እንቆማለን" በሚል መሪ ሃሳብ መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።
የመንግስትን ትክክለኛ እርምጃ አንዳንድ የውጭ አካላት የሚያደርጉትን ያልተገባ ዲፕሎማሲያዊ ጫናም አውግዘዋል።
ሰልፈኞቹ በፕሮግራሙ ማብቂያ ባወጡት ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አክራሪው የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን አጸያፊ ጥቃት እና የሀገር ክህደት ወንጀል አውግዘዋል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ መንግስት የወሰደው አፋጣኝ ህግ የማስከበር እርምጃ ኢትዮጵያን ከመበተን እንደታደገ እና ህግ ከማስከበር ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳልነበረም ገልጸዋል።
በአንዳንድ የህውሓት ርዝራዦች እና ደጋፊዎች እየተካሄደ ያለውን የሐሰት መረጃ ስርጭት እና ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም በአንዳንድ ሀገራት እና ድርጅቶች እየተሞከረ ያለውን ጫናም አውግዘዋል።
መንግስት ከህግ ማስከበሩ ጎን ለጎን በክልሉ በህወሓት የወደሙ የመሰረተ ልማቶችን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የወሰደውን እርምጃ እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ንጹሐን ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የወሰደውን እርምጃም አድንቀዋል።
በሱዳን የኢፌዴሪ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያዊያኑ ለሀገራቸው አንድነት ከመንግስታቸው ጎን በመቆም ያደረጉትን ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ አድንቀዋል።
ህወሃት ለውጡን ተከትሎ የበላይነቱን በማጣቱ ብቻ ሀገርን ለመበተን ክህደት መፈጸሙንም አስታውሰዋል።
ቡድኑ ከአነሳሱ ጀምሮ ትግራይን ገንጥሎ ነፃ አገር ለመመስረት ያለመ አገራዊ ራእይ የሌለው ጠባብ ቡድን መሆኑን ጠቅሰው፤ “ተሳክቶለት ቢሆን ኖሮ በሀገራችን እና በቀጠናው ሊፈጠር ይችል የነበረው አደጋ የከፋ ይሆን ነበር” ብለዋል።
ሆኖም በመንግስት ብልሃትና በሰራዊቱ ጥንካሬ በአጭር ጊዜ ሴራው ሊከሽፍ እንደቻለ አውስተዋል።
“ህግ የማስከበሩን ተግባር በብቃት ብንወጣም የህወሃት እርዝራዦች፣ ተከፋዮቻቸው እና አንዳንድ አካላት በቡድኑ ላይ ነፍስ ለመዝራት በአገራችን ላይ ያልተገባ ጫና በማድረግ ላይ ይገኛሉ” ብለዋል።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ዘብ መቆም እንደሚገባውና በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎችንም ማጋለጥና ማክሸፍ ይገባል ብለዋል።
በሱዳን ካርቱም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማዕከል በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች እና ወጣቶች ተሳትፈዋል።