የጊንጪ ኃይል ማከፋፈያ የምዕራብ ሸዋ ዞን አካባቢን በኢንዱስትሪና በግብርና ለማልማት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ... ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ - ኢዜአ አማርኛ
የጊንጪ ኃይል ማከፋፈያ የምዕራብ ሸዋ ዞን አካባቢን በኢንዱስትሪና በግብርና ለማልማት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ... ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ
መጋቢት 11/2013(ኢዜአ) የጊንጪ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የምዕራብ ሸዋ ዞን አካባቢ በኢንዱስትሪና በግብርና ለማልማት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ሲሉ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ።
ኤ.ዲ.ዲ.ኤም እና ጂ የተሰኘው የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት አካል የሆነውና 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት የጊንጪ ቁጥር ሁለት የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ መንግስት በሃይል ማመንጨት፣ ስርጭትና ተደራሽነት በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በውሃ፣ በፀሃይ፣ በነፋስና በሌሎች ታዳሽ ሃይል የሚመነጨውን ሃይል በአንድ ቋት በማስተሳሰር አሁን ካለው 4 ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል በሁለት ዕጥፍ ለማሳደግ እየሰተራ ነውም ብለዋል።
65 በመቶውን ሃይል በአንድ ኔትወርክ ወይም ቋት በማስተሳሰር 70 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን፣ 35 በመቶውን ደግሞ በተናጠል የሃይል አማራጮች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ 5 ዓመታት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ሃይል ብርሃን ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራች መሆኑንም ጠቅሰው፤ የሚመነጩ ሃይሎችን ወደ ውጤት መለወጥ የሚቻለው የማከፋፈያ ጣቢያዎችና የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ሲዘረጉ እንደሆነም አክለዋል።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው የጊንጪ ኅይል ማከፋፈያ ጣቢያም ኢንዱስትሪ ያልተስፋፋባቸው የምዕራብ ሸዋ ዞን ወረዳዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያው በአካባቢው ለሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች፣ ለመስኖ ልማትና ለመጠጥ ውሃ አገልግሎት መሰረተ ልማት አስተማማኝ ሃይል ማቅረብ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በቀጣይም ሽኩቴ በተባለ ስፍራ ሌላ ማከፋፈያ ጣቢያ እንደሚገነባ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በዞኑ ሌሎች ወረዳዎችን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በደንዲ ወረዳ ጊንጪ ከተማ አቅራቢያ የተገነባው ባለ 230/15 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያው፤ ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ተገጥመውለታል።
ላርሰን ኤንድ ቱርቦ የተሰኘ የሕንድ ኩባንያ ግንባታውን ያከናወነው ሲሆን፤ ኤም.ቪ.ቪ ዲከን የተባሉ የጀርመንና ስዊዘርላንድ ኩባንያ የማማከር ሥራውን ሰርተዋል።
ጊንጪ ቁጥር 2 ማከፋፈያን ጨምሮ 56 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የተደረገባቸው አቃቂ ቁጥር 2፣ ደብረዘይት ቁጥር 3፣ ዱከም ቁጥር ሁለትና ሞጆ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላርሰን ኤንድ ቱርቦ በተሰኘው የሕንድ ኩባንያ የተነገቡ ናቸው።
የጊንጪ የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለከተማዋና ለአካባቢው አስተማማኝ ሃይል ማቅረብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።