በሰለጠኑ ባለሙያዎች የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 50 በመቶ ደርሷል - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሰለጠኑ ባለሙያዎች የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 50 በመቶ ደርሷል - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11 ቀን 2013 (ኢዜአ) በሰለጠኑ ባለሙያዎች በመታገዝ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 50 በመቶ መድረሱን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
ለተገኘው ውጤት የሚድዋይፎች ሚና ጉልህ መሆኑንም አስታውቋል።የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር ለሁለት ቀናት የሚቆየውን 29ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው ላይ የጤና ሚኒስቴር፣ አጋር ድርጅቶችና የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባላት እየተሳተፉ ነው።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በጤና ባለሙያዎች በመታገዝ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እየጨመረ ነው።
እ.አ.አ በ2016 በጤና ባለሙያዎች ድጋፍ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 28 በመቶ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህ አሃዝ ወደ 50 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልፀዋል።
ከ30 ዓመታት በፊት በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው የሚያልፍ ሴቶች ቁጥር በየዓመቱ 30 ሺህ እንደነበር የጠቀሱት ዶክተር መሰረት፤ "አሁን ወደ 11 ሺህ ዝቅ ማድረግ ተችሏል" ብለዋል።
መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ለውጤቱ መገኘት ቁልፍ ሚና መጫወቱንና የሚድዋይፎች ሚናም ትልቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ 17 ሺህ ክሊኒኮች እና 400 ሆስፒታሎች መኖራቸውን ገልጸው፤ የጤና ተቋማት መስፋፋት ለተገኘው ውጤት ሌላው ምክንያት መሆኑን አክለዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ የጤና ሚኒስቴር በመስኩ የሚሰሩ ስራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቷል።
በተለይም በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ የእናቶችን ጤና ማሻሻል፣ የህጻናትና ጨቅላ ህጻናትን ሞት መቀነስ እና የአፍላ ወጣቶች ጤና ላይ የሚሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ዕድሜያቸው ለመውለድ ሳይደርስ የሚወልዱ በመኖራቸው ይህንን ለማስቀረት ግንዛቤ መፍጠር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
"የሚድዋይፎች ቁጥር ከበፊቱ የተሻለ ቢሆንም ከአገልግሎት ፈላጊው ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል" ብለዋል ዶክተር መሰረት።
የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዘነበ አካለ በበኩላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚድዋይፎች ቁጥር ከ17 ሺህ በላይ ደርሷል ብለዋል።
ይሁን እንጂ በቅርቡ በተደረገ ጥናት 40 በመቶ የሚሆኑት በስራቸው እርካታ የሌላቸው መሆኑን ያመላከተ ሲሆን ይህም በአገልግሎት ጥራት ላይ አሉታዊ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ የስራ እርካታ ለማምጣት መስራት ይገባል ነው ያሉት።
"አሁንም በአማካይ በየቀኑ 30 እናቶች በወሊድ ምክንያት ለህልፈት ይዳረጋሉ" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የበለጠ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
የፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር መንግሥቱ አስናቀ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሚድዋይፎች ጥራት ላይ መስራት ቁልፍ ጉዳይ ነው።
ሚድዋይፎችን ማሰልጠን ብቻውን በራሱ ግብ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ሙያተኞች በሰለጠኑበትና በገበዩት እውቀት ልክ እየሰሩ መሆኑን መከታተል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።