የኤሌክትሪክ ሀይል ማግኘት ያልቻለው ትምህርት ቤት በመማር ማስተማር ስራው ላይ ችግር ገጥሞታል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ሀይል ማግኘት ያልቻለው ትምህርት ቤት በመማር ማስተማር ስራው ላይ ችግር ገጥሞታል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11/2013(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም አፀደ ሕጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሶስት ዓመታት የኤሌክትሪክ ሀይል ማግኘት ባለመቻሉ የመማር ማስተማር ስራው ችግር እንደገጠመው አስታወቀ።
በቦሌ አራብሳ የጋራ መኖሪያ መንደር የሚገኘው ብቸኛው የመንግስት ትምህርት ቤት ኤሌክትሪክ የሚያገኘው ከግለሰብ ቤት መሆኑን ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ ችግሩ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል በተፈጠረ አለመጣጣም የተከሰተ በመሆኑ ለመፍትሄ እየሰራሁ ነው ብሏል።
ቅሬታውን ለኢዜአ ያቀረበው ትምህርት ቤቱ ከተመሰረተ ጀምሮ ላለፋት ሶስት ዓመታት የኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘት ባለመቻሉ የመማር ማስተማሩ ስራ መስተጓጎሉን አስታውቋል።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ጌትነት ገብረሚካኤል ትምህርት ቤቱ ከተመሰረተ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም የኤሌክትክ ሀይል ማግኘት እንዳልቻለ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ ከ7 ሺህ በላይ ተማሪዎች፣ ከ300 የሚበልጡ መምህራንና 86 ድጋፍ ስጪ ሠራተኞች እንዳሉት አብራርተዋል።
ይህ ትውልድ የሚገነባበት ተቋም ቅድሚያ ተሰጥቶት የኤሌክትሪክ ሃይል ሊሟላለት ሲገባ ይህ አልሆነም ሲሉ ርዕሰ መምህሩ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የኤሌክትሪክ ሀይል ባለመኖሩ ተማሪዎች በንድፍ ሀሳብ የተማሩትን በቤተ-ሙከራ በተግባር እንዳይሞክሩ እክል መፍጠሩን አስረድተዋል።
መምህራንም ተማሪዎችን ለማስተማር በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዳይሰጡ ከማድረጉም በላይ የራሳቸውን አቅም በቴክኖሎጂ ደግፈው እንዳያበቁ ተግዳሮት መሆኑንም አመላክተዋል።
ችግሩ እንዲፈታ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያቀርቡም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ነው የተናገሩት።
የትምህርት ቤቱ የፊዚክስ መምህር አዳነ ወርቁ የኤሌክትሪክ ሃይል ችግሩ እርሳቸው በሚሰጡት ትምህርት ተገቢውን እውቅት ለልጆቹ መስጠት እንዳልተቻለ ይናገራሉ።
ዘመኑ የሚጠይቀውን የኮምፒዩተርና መሰል የትምህርት መስጫ መሳሪያዎች ተጠቅሞ የተሻለ እውቅት ከማካፈል አንጻር ትምህርት ቤቱ ላለፋት ሶስት ዓመታት ትልቅ ችግር እንደገጠመው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የውስጥ ግኑኙነት ስራ አስኪያጅ አቶ ባዩ ለገሰ የተባለው ችግር መኖሩን አምነው በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል በተፈጠረ አለመጣጣም የተከሰተ ነው ብለዋል።
ጥያቄውና ቅሬታው ተገቢነት ያለው እንደሆነና ይህን ያህል ጊዜ መዘግየት እንዳልነበረበት ተናግረዋል።
ይሁንና ተቋማቸው ባለፈው አንድ ዓመት የውዝፍ ሰነዶች፣ የግዥና የኤሌክትሪክ ቁሳቁስ አቅርቦት ችግሮች እንደነበሩበት ገልጸዋል።
ለትምህርት ቤቱ የተጠየቀው የኤሌክትሪክ መጠን ባለ መቶ ኬቢ በመሆኑና ተጨማሪ ክፍያ በመጠየቁ መንግስት በራሱ አቅም ተጨማሪውን ወጪ ለመሸፈን ሲሰራ እንደነበረም ተናግረዋል።
በአጭር ጊዜ ትምህርት ቤቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆንና ለዚህም ወደ እንቅስቃሴ መግባታቸውን ገልጸዋል።