ቀጥታ፡

"መሪና ተመሪው" መጽሐፍ ለምረቃ በቃ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፈተናዎች ላይ ያተኮረው የመልዓከ ሠላም ዶክተር አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ መጽሀፍ ተመረቀ።

በመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መጽሐፋቸውን ያስመረቁት መልዓከ ሠላም ዶክተር አባ ቃለጽድቅ መጽሐፉ ቤተክርስቲያንና ክፍለ ዘመኑ ሊኖራቸው ስለሚገባው የመሪነት ሚና እንደሚያብራራ ገልፀዋል።

ሰው በማንነቱ ሳይሆን በሙያውና በዕውቀቱ እንዴት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ለማስረዳት መጽሐፉን እንደፃፉትም ተናግረዋል።

በተለይ ቤተክርስቲያን ልዩልዩ የሃይማኖት፣ የሥነጥበብና በተለያዩ ርዕሶች የተፃፉ መፅሃፍት ቢኖሯትም በአመራርና አስተዳደር ላይ አተኩረው የተፃፉ ባለመኖራቸው መጽሐፉን እንደፃፉት አስረድተዋል።

መሪና ተመሪው መፅሃፍ ትውልዱ ባልሆነ ትርክት እየሄደ የተሳሳተ መንገድ ላይ እየወደቀ ስለሆነ መንፈሳዊ አባቶችና በተለያየ ዘርፍ ያሉ አመራሮች እንዴት እንደሚመሩ ለማመላከት መሞከሩን ጠቁመዋል።

በመጽሐፉ ምርቃት ላይ ተገኝተው ሂስ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ምናሴ ወልደሃና መጽሐፉ የአመራር ጥበብ መነሻ ቤተክርስቲያን መሆኗን ያሳያል ብለዋል። 

ለዚህም የዘመናዊው አስተዳደር አባት የሚባለው ዊስሎ ቴለር በኦሪት ዘፀዓት ምዕራፍ 18 ያለውን የሙሴን ታሪክ እንደመነሻ በመውሰድ መጥቀሱ የአስተዳደር መነሻ መጽሐፍ ቅዱስና ቤተክርስቲያን መሆኗን ያሳያል ነው ያሉት። 

በጠቅላይ ቤተክህነት የውጭ ጉዳይ መምሪያ ዋና ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤልም ብዙ መጻሕፍት መሪነት ላይ አተኩረው እንደተፃፉና ይህ ግን መሪንና የመሪነት ጥበብን አጣምሮ መያዙን ገልፀዋል።

ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻልም መጽሐፉ ያመላክታል ያሉት መምህር ዳንኤል መጽሐፉ ተቋማዊ መፍትሔ እንዴት እንደሚመጣ ማብራራቱ ወቅታዊ ያደርገዋል ብለዋል።

"መሪና ተመሪው" መጽሐፍ በአምስት ክፍሎችና በ18 ምዕራፎች የተከፈለና 190 ገፆች ያሉት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም