ቀጥታ፡

"ሠብዓዊነትና ፍቅር ለትግራይና መተከል" ጥምረት በጋሌሳ ቀበሌ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የመጀመሪያውን ዙር ድጋፍ አደረገ

መጋቢት 11/2013(ኢዜአ) "ሠብዓዊነትና ፍቅር ለትግራይና መተከል" ጥምረት በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኩል በድባጤ ወረዳ ጋሌሳ ቀበሌ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሠብዓአዊ ድጋፍ አድርጓል።

"ሠብዓዊነትና ፍቅር ለትግራይና መተከል" ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባላትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ በስፍራው በመገኘት ድጋፉን አበርክተዋል።

የሠብዓዊነትና ፍቅር ለትግራይና መተከል ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ወይዘሪት ሜሮን ታደለ በጋሌሳ ቀበሌ እየተደረገ ያለው ድጋፍ መላው ኢትዮጵያዊያን ለተፈናቃዮች አብሮነታቸውን ለማሳየት መሆኑን ገልጻለች።

ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጋሌሳ ቀበሌ ለሚገኙ ወገኖች የተደረገው ድጋፍ 500 ኩንታል ዱቄት እና 3 ሺህ 340 ሊትር ዘይት እንደሆነም ተናግራለች።

የመጀመሪያውን ዙር ድጋፍ በጋሌሳ ቀበሌ ለማድረግ የተፈለገው በፀጥታ ችግር ምክንያት በቂ ድጋፍ ባለመደረጉ ነው ያለችው፤ ወይዘሪት ሜሮን ድጋፉ በቀጣይ ዙርም እንደሚቀጥል ነው ያስታወቀችው።  

የድጋፍ ስርጭቱን እያከናወነ ያለው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቤኒንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽባባው አሰጌ ኮሚቴው ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ያደረገው የሃብት ማሰባሰብና የስርጭት ስራው በማኅበሩ እንዲከናወን ማድረጉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ድጋፉ በአካባቢው ያለውን ችግር እንደሚያቃልልና ስርጭቱም ተፈናቃዮች ባላቸው የቤተሰብ ቁጥር በመለየት እየተከናወነ መሆኑን አቶ ሽባባው ገልፀዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ተፈናቃዮች በበኩላቸው ኮሚቴው ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ በመረዳት ላደረገላቸው ድጋፍ  አመስግነዋል።

"ሠብዓዊነትና ፍቅር ለትግራይና መተከል" በሚል ሃሳብ በአርቲስትና የሠብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ መሪነት ግሎባል አሊያንስ የሠብዓዊ ድጋፍ ጥምረት፣ የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሠብዓዊ መብቶች ማኅበር፣ ለትግራይ እርዳታ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኛ፣ ለመተከል እርዳታ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኛና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በጋራ ያሰባሰቡትን ሃብት በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም