ቀጥታ፡

በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የማህበረሰቡን ግንዛቤና ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

ቢሾፍቱ፣ መጋቢት 11/2013 ( ኢዜአ ) በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ማህበረሰቡ ያለውን ግንዛቤና ተጠቃሚነት የሚያሰፋ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በ1986ዓ.ም ወጥቶ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረውን ፖሊሲ ለተሻለ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በ2004ዓ.ም በማሻሻል በተግባር አውላለች። 

በፖሊሲው የተግባር ሂደት በርካታ ውጤቶች ቢመዘገቡም መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት ረገድ ግን ጉድለቶች መታየታቸውን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ቀድሞ በግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው የልማት እድል በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ቱሪዝም፣ ማዕድንና አይሲቲን አዳዲስ የልማት ትኩረት አድርጎ በተግባር በማዋል በዘርፉ ነባራዊውን ዓለም የዋጀ የፖሊሲ ማሻሸያ አስፈልጓል።

የተሻሻለውን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ በባለድርሻ አካላት ለማስገምገም የተዘጋጀ የውይይት መድረክም በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ ረቂቅ ፖሊሲውን ለባለድርሻ አካላት ያቀረቡት የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርና የፖሊሲው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ጌታቸው ናቸው።

አቶ ሰለሞን እንዳሉት የበለጸጉ አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተገቢው ማዋላቸው በተግባር የሚገለጽ ነው።

“በመሆኑም ፈጣንና ተለዋዋጭ የሆነውን የዘርፉን ምህዳር ለመፍጠርና በትግበራ ሂደት የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ታስቦ አገራዊው ፖሊሲው ማሻሻል አስፈልጓል”ብለዋል። 

አገሪቷ በዘርፉ የላቀና በዓለም ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ያላት ቢሆንም በማህበረሰቡ ደረጃ በዘርፉ ያለውን ሰፊ የግንዛቤ ክፍተት የሚሞላ ስነ ምህዳር መፍጠርና የንቅናቄ ስራ መስራት ፖሊሲው ያስፈለገበት ዋና ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ አቶ ሰለሞን።

“ወቅቱ የሚጠይቀውን "የዲጂታል ኢኮኖሚ ፈጥረን መሄድ ካልቻልን ከዓለም መወዳደር ቀርቶ ለመኖርም አዳጋች ጊዜ ላይ ደርሰናል" የሚሉት ደግሞ በመድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፎዚያ አሚን ናቸው።

“በመሆኑም የማህበረሰብ ንቅናቄ ስራው በስፋት ይሰራበታል” ብለዋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የሚዲያና ፕሬስ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አለምነው በበኩላቸው በዘርፉ በተለይም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች የሚያስተናግድ ምህዳር መፍጠሩ ላይ የነበሩት ችግሮች በፖሊሲው መለየታቸውን ነው የሚናገሩት።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በሲዳማ ክልል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ የአይሲቲ ልማት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ እንዳሉትም የተሻሻለው ፖሊሲ በተለይም ለሰው ሃይል ግንባታ ትኩረት ሰጥቷል።

በመድረኩ የተገኙት ባለድርሻ አካላትም ፖሊሲውን ለማስፈጸም ትልቅ ሚና ያላቸው፣ የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ባለሙያዎች እንዲሁም በክልሎች የተቋቋሙ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽኖች ተወካዮች ናቸው።

ሰፊ የቡድን ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን ለተነሱት አስተያየቶችና የግልጽነት ጥያቄዎች በረቂቁ አዘጋጅ ቡድን አባላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ከባለድርሻ አካላት በተገኙ አስተያየቶች ግብዓትነት ረቂቅ ፖሊሲው ተሻሽሎ በሚመለከተው አካል የሚጸድቅ ይሆናል።

የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ እንዲሁም ከአይሲቲ ፖሊሲ ጋር ተደጋጋፊ ፖሊሲ ሆኖ ይተገበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም