የጊንጪ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጊንጪ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተመረቀ
መጋቢት 11/2013/ኢዜአ/ በ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የጊንጪ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተመረቀ።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ኤ.ዲ.ዲ.ኤም እና ጂ የተሰኘው ፕሮጀክት አካል የሆነው የጊንጪ የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ነው የተገነባው።
የማከፋፈያ ጣቢያው ኃይል የሚያገኘው ከገፈርሳ - ጌዶ ከተዘረጋው ባለ 230 ኪ.ቮ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ሲሆን ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ተተክለውለታል፡፡
የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያው 230/15 ኪሎ ቮልት ሲሆን ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ተገጥመውለታል።
እስከ 100 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ሲኖረው አስር ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮችም አሉት።
ላርሰን ኤንድ ቱርቦ የተሰኘ የሕንድ ኩባንያ ግንባታውን ያከናወነው ሲሆን፤ ኤም.ቪ.ቪ ዲከን የተባሉ የጀርመንና ስዊዘርላንድ ኩባንያ የማማከር ሥራውን ሰርተዋል።
ላርሰን ኤንድ ቱርቦ የሚገነባቸው አራት የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች አቃቂ ቁጥር 2፣ ደብረዘይት ቁጥር 3፣ ዱከም ቁጥር ሁለትና ጊንጪ ቁጥር 2 አጠቃላይ ግንባታቸው 56 ሚሊዮን ዶላር ነው።
የጊንጪ የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለከተማዋና ለአካባቢው አስተማማኝ ሃይል ማቅረብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።