ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድቡ የተጀመረበትን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጀ

አሶሳ፤ መጋቢት 11 /2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡

በክልሉ የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታነህ ሰዲ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የህዳሴው ግድብ ድጋፍ ማሰባሰብ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከመደበኛው የገቢ ማሰባሰብ ስራ በተጓዳኝ የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም መዘጋጀቱን  ገልጸዋል፡፡

በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከሚከናወኑ የገቢ መሰባሰቢያ ፕሮግራ መካከል የቦንድ ሽያጭ ዋነኛ እንደሆነ ጠቅሰው ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል፡፡

ከቦንድ ሽያጩ በተጨማሪ በስጦታ የሚበረከቱ ገንዘቦችንም ማሰባሰብ እና "አሻራዬን አኑሪያለሁ"የሚል መልዕክት ያለው የደረት  "ፒን"  ጨምሮ ሌሎች መርሃ ግብሮች እንደተካተቱ ጠቁመዋል፡፡

ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ የክልሉ ህዝብ 80 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አቶ ጌታነህ አስታውሰዋል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የቦንድ ሽያጭ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ልማት ባንክ፣ ብድር እና ቁጠባ ተቋማት እና ከክልል እስከ ቀበሌ የሽያጭ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ቦንድ በመግዛት ግድቡ እውን እንዲሆን ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከአሶሳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሰቦቃ አብዲሳ በሰጡት አስተያየት  ያደጉ ሃገራት ሚስጥር በሃገራዊ ጉዳዮች አንድ መሆናቸው ነው ብለዋል፡፡

አባይ ሲገደብ የኢትዮጵያዊያን ህይወት እንደሚለወጥ የተናገሩት አስተያየት ሰጪው ጥቃቅን ልዩነታችንን ትተን ባለን አቅም ለግድቡ ተሳትፏችንን ማሳደግ ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ግድቡን ለማደናቀፍ በሃገር ውስጥ እና ውጭ የሚደረግ ተደጋጋሚ ሙከራዎች እንደሚቃወሙ የተናገሩት ደግሞ አቶ አብዱራህማን ኡስማን  ናቸው፡፡

የግድቡ ስራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ እንደማይቀርና ለትውልድ የሚተላለፍ ወሳኝ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፕሮጀክቱን መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

አቶ መሐመድ ኢብራሂም በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ በሃገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን በማሳደግ የስራ እድል እንዲፈጠር ዋነኛ ሚና ይጫወታል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ የእኛ ነው፤ ሀብታችን ነው ያሉት አቶ መሐመድ፤ በተለይ የሃገሪቱ ወጣት ፕሮጀክቱ የራሱ መሆኑን ተገንዝቦ ከፍጻሜ እንዲደርስ ድጋፉን መቀጠል እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል፡

ፕሮጀክቱ ከፍጻሜ እስኪደርስ ቦንድ ከመግዛት ጀምሮ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ነዋሪው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም