የህዝቦችን ሰላምና አንድነት ለማጠናከር ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝቦችን ሰላምና አንድነት ለማጠናከር ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም እንደሚገባ ተመለከተ
ሚዛን ፤ መጋቢት 11/2013( ኢዜአ ) በደቡብ ክልል የሚገኙ ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ሰላምና አንድነት ለማጠናከር ያሏቸውን ባህላዊ እሴቶች በማልማት መጠቀም እንደሚገባ ተመለከተ።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ "ባህላችን ለሰላማችንና ለአብሮነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲና ቤንች ሸኮ ዞን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የባህል ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው።
በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው ሲምፖዚየም መድረክ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አቡቶ አኒቶ እንዳሉት ክልሉ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚኖርበት በመሆኑ የብዙ ቱባ ባህል ባለቤቶች ናቸው።
"በየብሔረሰቡ የሚተገበሩ እነዚህ የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች የግጭት አፈታት ስርዓት ያላቸው ናቸው" ያሉት አቶ አቡቶ እስካሁን ከቀደሙት አባቶች የተወረሱ ባህላዊ እሴቶችን ዜጎችን ብሎም ሀገሪቱን ከጥፋትና ግጭት መታደጋቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ ለዘመናት ሲተገበሩ የቆዩ እሴቶች በመጤ ባህል እየተዋጡ በተለይ ወጣቱ እሴቶቹን በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ እንደ ኋላ ቀር ምልክት አድርጎ እየወሰደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ችግሩን ለማቃለል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መልካም እሴቶቻችን በጥናት ለይተው በማልማት ለትውልድ ማስተላለፍ ፣ የቆየ አብሮነትና ሰላምን ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋዎች የሚነገርባት፣ የጥበብ እና ቅርስ እንዲሁም ባህላዊ እሴት ባለቤት እንደሆነች ገልጸዋል።
ባህላዊ እሴቶቻችን ፍቅርና አብሮነትን፣ በህዝቦች መካከል መቻቻልን፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ አብሮ መኖርን የሚያጎለብቱ ናቸው ብለዋል።
እነዚህን የባህል ሀብቶች በምርምርና ጥናት አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ በዞኑ የሚገኙ ብሔረሰቦች መልካም ተጽዕኖ መፍጠር የሚያስችሉ እሴቶች ባለቤት ቢሆኑም በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር በተገቢው አልሰራንም ብለዋል።
በሲምፖዚየሙ ከሁሉም የክልሉ ብሔር ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተውጣጡ ተወካዮች እንዲሳተፉ መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳለ ወልደአማኑኤል ናቸው።
"ባህል የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር፣ ለአብሮነትና ወንድማማችነት ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው፤ ከዚህም ለባህል ልማትና ምርምር የሚያግዝ ግብዓት ይገኝበታል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሲምፖዚየም ባህላዊ እሴቶችን ለማሳደግና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል አቅጣጫ እንደሚቀመጥና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።