የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት እየሰራሁ ነው ... ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት እየሰራሁ ነው ... ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን
መጋቢት 11/2013(ኢዜአ) በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያነሱ ቅሬታዎችን ከመሰረቱ በመፍታት የዜጎችን እርካታ ለመጨመር እየሰራ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ረቂቅ ፖሊሲ ማበልጸጊያ አውደ ጥናት በአዳማ እየተካሄደ ነው።የሲቪል ሰርቪስኮሚሽን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ቀድማ የመንግስት አገልግሎት መስጠት መጀመሯን አንስተዋል።
ይሁንና በአገልግሎት አሰጣጡ በሚታዩ በርካታ ችግሮች ምክንያት ዜጎች በአገልግሎቱ እርካታ የላቸውም ብለዋል።
በተቋማት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለዜጎች እርካታ ማጣት ምክንያት መሆናቸውን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት የተለያዩ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
የመንግስት አገልግሎት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ጥናት በማካሄድ ችግሮቹን መፍታት ከስራዎቹ አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በረቂቅ ፓሊሲው አውደ ጥናት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የመጡ የሲቪል ሰርቪስ አመራሮችና እንግዶች ታድመዋል።