የኮቪድ-19 ክትባት መድኃኒት የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት አያስከትልም - ባለሥልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የኮቪድ-19 ክትባት መድኃኒት የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት አያስከትልም - ባለሥልጣኑ
አዲስ አበባ መጋቢት 10/2013 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ እየተሰጠ ያለው የኮቪድ-19 ክትባት የሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት የከፋ አለመሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ገለፀ።
ባለሥልጣኑ አስቸኳይ የጤና ችግር ሲያጋጥም የገበያ ፈቃድ ያልተሰጣቸውና ግምገማ ያልተደረገባቸውን መድኃኒቶች በመፈተሽ ፈቃድ ይሰጣል።
የባለሥልጣኑ የመድኃኒት ፈቃድ አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ አብደላ ጦሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአገሪቷ እየተሰጠ ያለው የኮቪድ ክትባት የፈቃድ አሰጣጡን የአፈጻጸም መመሪያ መስፈርት ያሟላል ብለዋል።
ክትባቱ እንደ ማንኛውም መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያስከትል ይችላል ያሉት ዳይሬክተሩ ከእነዚህም መካከል ብርድ ብርድ ማለት፣ ድካም፣ ራስ ምታት፣ ትኩሳትና የመገጣጠሚያ ሕመም እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
ክትባቱን እስካሁን ከ1 ሺህ 400 በላይ ለሆኑ ሰዎች መሰጠቱንና ከነዚህም በ35 ሰዎች ላይ የሚጠበቅ የጎንዮሽ ጉዳት ሪፖርት መደረጉን ገልጸዋል።
ይሁንና ኅብረተሰቡ ክትባቱ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ካለው ፋይዳና የጎንዮሽ ጉዳቱም የከፋ ባለመሆኑ መደናገጥ እንደማይገባው ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
የክትባቱን ደህንነት ለመከታተልና በሚፈለገው ፍጥነት እርምጃ ለመውሰድ የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።
ክትባቱን ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማዳረስ ከቻይና መንግሥት ተጨማሪ ክትባት ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ክትባቱ ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጥ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት አግኝታለች።