ቀጥታ፡

የህወሃት ጁንታ ቡድን ለስደተኞች የሚደረገውን ድጋፍ ሲያደናቅፍ መቆየቱ ተገለጸ

መጋቢት 10/2013(ኢዜአ)የህወሃት ጁንታ ቡድን በትግራይ ክልል በሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ስደተኞች የሚደረገውን የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደናቅፍ መቆየቱን የኢትዮጵያ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በዴቪድ ሊ ከሚመራው የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ኮሙዩኒኬሽን አሊያንስ ከተሰኘ ድረገጽ የጥያቄና መልስ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ የስደተኞች አያያዝ እና ወቅታዊ ጉዳይን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም በትግራይ ክልል የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ስደተኞች የሚደረገውን የሰብዓዊ ድጋፍ የህወሃት ጁንታ ሲያደናቅፍ መቆየቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት ለሚመጡ ስደተኞች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ከተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ስደተኞች ከስጋት አካባቢዎች ወደ ሌሎች ሰላማዊ አካባቢዎች ለማስፈር በሚደረገው ጥረት የትራንስፖርት እና የጥበቃ አገልግሎት እየሰጠ በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ ህግ ያላት እና በዚህም ስደተኞችን ስታስተናገድ የቆየች ሀገር መሆኗን የገለጹት አቶ ተስፋሁን፤ ከጎረቤት ሀገራት በስደት የሚመጡ ሰዎችን በማስተናገድ ረገድ ረጅም ልምድ አላት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እየተጠቀመች ያለችው የስደተኞች ህግ ስደተኞች ከመጠለያ ጣቢያ ውጭ የመኖር ዕድል የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም ትግራይን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑን ጠቅሰው፤ በርካታ ህጻናትና ወጣት ስደተኞችም ከኢትዮጵያውያን ጋር ተቀላቅለው የመደበኛና የከፍተኛ ተቋማት ትምህርታቸውን በሃገሪቱ ባሉ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየተከታተሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አንድም የኤርትራ ስደተኛ በሀይል ወደ ሀገሩ እንዲመለስ እየተደረገ አለመሆኑን ገልጸው፤ስደተኞች በሚኖሩባቸው በረሃማና ጠረፍ አካባቢዎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ በትግራይ ክልል ሲካሄድ የነበረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በወቅቱ ጣቢያዎቹ ውስጥ ለሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ባለመቻሉ ስደተኞቹ የአማራ ክልል እና አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሊሄዱ ችለዋል ብለዋል፡፡

የተበታተኑትን ስደተኞች አሰባስቦ ወደ ተሻለ ቦታ ለማስፈርና ከህብረተሰቡ ጋር ለመቀላቀል በማሰብ ከድንበር አቅራቢያ ያሉት ህጻጽና ሽመልባ ጣቢያዎች እንዲዘጉ ስለማድረጉ ያብራሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞችን ወደ ኤርትራ አስገድዶ የሚመልስበት አሳማኝ ምክንያተ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ የስደተኛ መጠለያዎች መጀመሪያውኑ ለኑሮ ምቹ ባለመሆናቸው ስደተኞቹ መታወቂያቸውን እስኪወስዱ ጠብቀው ከጣቢያዎቹ ጠፍተው ይሄዱ እንደነበር አስረድተው የህወሃት አስተዳደር ስደተኞቹ ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ባለመፈለጉ በርካታ እንቅፋት ሲፈጥር መቆየቱንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም