በኢትዮጵያ ለፓስታና መኮሮኒ የሚሆኑ የስንዴ ዝርያዎች እያነሱ መጥተዋል - ጥናት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለፓስታና መኮሮኒ የሚሆኑ የስንዴ ዝርያዎች እያነሱ መጥተዋል - ጥናት
አዲስ አበባ መጋቢት10/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለፓስታና መኮሮኒ ምርቶች የሚውሉ የስንዴ ዝርያዎች እያነሱ መምጣታቸውን አንድ ጥናት አመለከተ።
ከውጭ የሚገባውን የፓስታና መኮሮኒ ስንዴ ለመተካት ጥረቱ እንዲጠናከርም ተጠይቋል።
ዓለም አቀፉ የበቆሎ እና ስንዴ ምርምር ማዕከል በዝርያዎቹ ላይ ባካሄደው የዘረመል ምርምር ውጤት ላይ ዛሬ ዓውደ ጥናት አካሂዷል።
ምርምሩ የግብርና ምርምር ማዕከላትን፣ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲና ሌሎች ባለድርሻዎችን ማካተቱ ተገልጿል።
ለአምስት ዓመታት የተተገበረው ምርምር የተሻሻሉ ዝርያዎች አርሶ አደሩን ምን ያህል እየጠቀሙት ነው? ምን ያህል ውጤትስ ተገኝቶበታል? በቀጣይ ምን መደረግ አለበት? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሞከረ ተመላክቷል።
የዓለም አቀፉ የበቆሎ እና ስንዴ ምርምር ማዕከል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ክንዴ ተስፋዬ እንዳብራሩት በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው ምርምር ከ13 ሺህ በላይ የስንዴና የበቆሎ ናሙናዎች ተሰብስበውበታል።
በዚህም መሰረት ሦስት ጊዜ በስንዴ፣ በሁለት ዙሮች ደግሞ በበቆሎ ላይ ምርምር ተካሂዷል ብለዋል።
ከምርታማነት ጋር በተያያዘ በተለይም የተዳቀለ የበቆሎ ዝርያ የሚዘሩ አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን ምርምሩ ያሳየ ሲሆን መንግስት የተዳቀለ የበቆሎ ዘር በብዛት ለአርሶ አደሩ ማቅረብ እንዳለበት የሚያመላክት ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል አገር በቀሉ የፓስታና መኮሮኒ ስንዴ ዝርያ እየሰፋ መሄድ ሲጠበቅበት የምርምር ውጤቱ ግን በአርሶ አደሩ ዘንድ እጥረት መኖሩን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ1960ዎቹ እስከ 80 በመቶ ይደርስ የነበረው የስንዴ ዝርያ አሁን ላይ 10 በመቶ ብቻ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ ሲሉ ነው ያስረዱት አስተባባሪው።
የዳቦ ስንዴን በተመለከተ በአርሶ አደሩ ዘንድ በስፋት የሚገኝና ጥሩ ምርት እየሰጠ እንደሆነም ተናግረዋል።
"ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ፓስታና መኮሮኒ ለማስገባት ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሬ ታወጣለች" ያሉት ዶክተር ክንዴ ከውጭ የሚገባውን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚመለከታቸው አካላት መረባረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በተለይም የፓስታና መኮሮኒ ስንዴ የዘር ስርጭት፣ ኤክስቴንሽንና ምርምሩ ላይ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በምርምር የወጡ የፓስታና መኮሮኒ ስንዴ ዝርያዎች በአግባቡና በብዛት አርሶ አደሩ ጋር የሚደርሱበት ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነም አመልክተዋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው የምርምር ውጤቱ ሳይንሳዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ በቀጣይ ለፖሊሲ ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ማንደፍሮ ገለጻ በግብርናው ላይ ውጤታማነትን የሚያሳድጉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች የተጀመሩ በመሆኑ የምርምር ውጤቱ እንቅስቃሴውን እንደሚደግፍ ጠቁመዋል።
በቀጣይ ለሚሰሩ የምርምር ስራዎች መሰረት እንደሚጥልም አክለዋል።