ቀጥታ፡

ለውጥን የማይቀበሉ ኃይሎች የሚያደርሱትን ሰብአዊ ጉዳት ለመከላከል መንግስት ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ ይገባል-የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

ደሴ ሀምሌ 21/2010 ህዝባዊ ለውጦችን የማይቀበሉ ኃይሎች ሊፈጥሩት የሚችሉትን ሰብአዊ ጉዳት ለመከላከል መንግሥት ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ በደሴ ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ ነዋሪዎቹ በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዘው መንግስት የግድያውን መንስኤ በፍጥነት በማጣራት የድርጊቱ ፈጻሚዎችን ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል ። ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ መኪያ አወል "ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጎዳና አብዛኛው ህዝብ እየደገፈው ቢሆንም በለውጡ ደስተኛ ያልሆኑ ግለሰቦች ሰብአዊ ጉዳት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው" ብለዋል ። "በኢንጂነር ስመኘው ላይ በአደባባይ የደረሰው ግድያ ማሳያ ነው" ሲሉም ገልጸዋል ። ብዙኃኑን ያስማማ ለውጥን የሚቃወሙ ጥቂት ግለሰቦች የሚፈጽሙትን ህገ ወጥ ድርጊት መንግሥት የማያዳግም ርምጃ በመውሰድ ለውጡን ማስቀጠልና የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚገባውም  ወይዘሮ መኪያ አመልክተዋል። አቶ ሽመልስ ይማም በበኩላቸው "በኢንጀነር ስመኘው ላይ የተፈፀመው ግድያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሜሪካ ላይ የሚኖራቸው ቆይታ እንዲደበዝዝ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ አሳፋሪ ድርጊት ነው" ብለዋል፡፡ በኢንጅነሩ ላይ የተፈጸመው ግድያ የህዝብ ተቀባይነት ያላቸው ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና ምሁራን አስፈላጊው የደህንነት ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያስተምር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ "መንግሥት በኢንጅነሩ ላይ የተፈፀመውን ግድያ በፍጥነት በማጣራት ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን ለህግ በማቅረብ የህዝቡን እምባ ማበስ ይገባዋል" ያሉት ደግሞ አቶ እንድሪስ አደም ናቸው፡፡ "የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ በማጠናቀቅ የኢንጂነር ስመኘውን ስም ህያው ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል" ያሉት ነዋሪዎቹ ለኢንጅነሩ ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም