በአማራ ክልል በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ 131 የገጠር ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የይዞታ ማረጋገጫ አገኙ

ባህርዳር ፤ መጋቢት 10 /2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ 131 የገጠር ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ መደረጉን የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ገለጸ።

የይዞታ ማረጋገጫ መሰጠቱ የስፖርት ማዝውተሪያ ስፍራዎችን ህጋዊነት ለማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑን በኮሚሽኑ የስፖርት መሰረተ ልማት ዳይሬክተር አቶ ባምላክ ሙላት ለኢዜአ ተናግረዋል ።

በክልልና ዞን ደረጃ የሚገኙት ከፍተኛና መካከለኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራያዎች ላይ በአንጻራዊነት የህጋዊነት ችግር እንደማይስተዋልባቸው ጠቁመዋል።

በወረዳና ቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የማዘውተሪያ ስፍራዎች የሚሰጡትን ጥቅም ባለመገንዘብ የየአካባቢው አስተዳደር ያለምትክ ቦታ ለኢንቨስትመንትና ለሌሎች አገልግሎቶች በመስጠት ችግር መፈጠሩን አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገው ጥረት በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ 131 የገጠር ስፖርት ማዘውሪያ ስፍራዎች የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

በየደረጃው ለሚገኙ የስፖርት ጽህፈት ቤቶች በባለቤትነት እንዲያስተዳድሩት የይዞታ ማረጋገጫው የሰጡት የቀበሌዎች መሬት አስተዳደር ክፍሎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት 400 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተዘጋጅተው ለአካባቢያቸው ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ መመቻቸታቸውንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ይህም ወጣቱ በቅርበት ስፖርታዊ ልምምዶችን፣ ውድድሮችንና ስልጠናዎችን እንዲያገኝ በማድረግ በየደረጃው ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በሚያስችል መልኩ እየተፈጸመ ነው ብለዋል።

የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በይዞታ ማረጋገጫ ደብተርና ካርታ የተደገፈ ህጋዊነት እንዲኖራቸው ማድረጉ ለመጪው ትውልድ ጭምር ለማስተላለፍ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የስፍራዎቹን ህጋዊነት በማረጋገጥ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉም በየደረጃው ለሚገኘው አመራር ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን ጠቁመው በቅርቡም በክልሉ ከፍተኛ አመራር የሚመራ መድረክ እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡

በባህርዳር የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ነዋሪው ወጣት ሙሉቀን አለሙ በሰጠው አስተያየት ፤ ወጣቱ በአስፓልት ላይ ስፖርት በመስራትና በመለማመድ ለትራፊክ አደጋ እንዳይጋለጥ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በየቀበሌው ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተናግሯል።

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ሰናይት አዲሱ እንዳለችው የማዘውተሪያ ስፍራዎች ተደራሽ መሆን ወጣቱን በአካልና አእምሮ ዳብሮ መልካም ስብዕናን ተላብሶ እንዲያድግ ያግዛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም