ቀጥታ፡

ቦርዱ ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው... የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች

  አዲስ አበባ መጋቢት 10/2013 /ኢዜአ/ ምርጫ ቦርድ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በገለልተኝነት ለማካሄድ ያከናወናቸው ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ገለጹ።

ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚከናወኑ ቅስቀሳዎች ከግለሰብ ይልቅ ሃሳብ ላይ ያተኮሩ መሆን እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

6ኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ተስፋ ተጥሎበታል።

ምርጫው እንደከዚህ ቀደሙ 'የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት  ጥያቄዎች'  በሚሉ ሀሳቦች ላይ ብቻ  ያተኮረ ሳይሆን የአገሪቷን ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች በመሰረታዊነት በመፍታት ረገድ  ትልቅ ዕድል እንዳለውም በርካቶች  ይስማማሉ።

ምርጫውን በማከናወን ረገድ ትልቁ ኃላፊነት የተሰጠው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ እንደ አዲስ ተደራጅቷል።

ቦርዱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቋማዊ መዋቅሩን ከማደራጀት ጎን ለጎን ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ፓርቲ የዕጩ ምልመላ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኢዮብ መሳፍንት ኢትዮጵያ ከነበረችበት የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ የሚከናወኑ ተግበራት ፈታኝ መሆናቸውን እንደሚገነዘቡ ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ ከተደራጀ በኋላ ምርጫውን በገለልተኝነት ለማካሄድ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል።

ይህም 6ኛው አገራዊ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተደረጉት ምርጫዎች የተለየ እንደሚያደርገው ነው የተናገሩት።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጣሂር መሃመድም ቦርዱ በአጭር ጊዜ ራሱን በሰው ሃይል በማደራጀትና ተቋማዊ አሰራሩን በማዘመን ምርጫውን ለማካሄድ የሄደበትን ርቀት አድንቀዋል።

ቦርዱ በእስካሁኑ ሂደትም ገለልተኛ በሆነ መልኩ በምርጫው ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ጠንካራ የእርስ በእርስ ግንኙነት መፍጠሩን ገልፀዋል።

ነገር ግን እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ባሉ አደረጃጀቶቹ ወጥነት ያለው አሰራር በመፍጠር ረገድ አሁንም ውስንነቶች እንዳሉበት ነው የጠቆሙት።

'6ኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ሲሹት የነበረውን እውነተኛ ምርጫ የሚያሳኩበት ነው' ያሉት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ ዛዲግ አብርሃ ናቸው።

አቶ ዛዲግ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትም ሆኑ መራጩ ሕዝብ ምርጫው በአግባቡ እንዲከናወን በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ከሚሳተፉ ፓርቲዎች ጋር በየጊዜው በመገናኘትና ስራዎችን በመገምገም  ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ እያከናወነ ላለው ተግባርም ምስጋና አቅርበዋል።

የፓርቲዎቹ ተወካዮች በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚከናወኑ ቅስቀሳዎች ግለሰብ ላይ ትኩረት ከማድረግ ወጥተው ለመራጩ ሕብረተሰብ የሃሳብ ገበያ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአባሎቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው በምርጫው ትክክለኛ ዓላማና አካሄድ ላይ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

"እኛና እነሱ" የሚል ቡድን የመፍጠር አካሄድ የምርጫውን ትክክለኛ ዓላማ እንደሚያስትም አብራርተዋል።

መደበኛ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች በገለልተኝነትና ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል በማስተናገድ በማኅበራዊ ሚዲያ አሉባልታዎችን በመቀነስ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ምርጫ ቦርድ በቅርቡ በምርጫው ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ባካሄደው ውይይት የዕጩ ምዝገባ ሂደቱን በሚመለከት ከፓርቲዎች የቀረቡለትን ከ500 በላይ ቅሬታዎች በአፋጣኝ እንደፈታ መግለጹ ይታወሳል።

በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የዕጩዎች ስምና የመወዳደሪያ ምልክት አቀማመጥ ቅደም ተከተል በሎቶሪ ዕጣ እንደሚወሰንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም