የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ያሠለጠናቸውን 64 ተማሪዎች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ያሠለጠናቸውን 64 ተማሪዎች አስመረቀ
አምቦ ሀምሌ 21/2010 የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ከክርስቲያን በጎ አድራጎት ማህበር ኮንሶርቲየም ጋር በመተባባር በዴቬሎፕመንታል ማኔጅመነት የትምህርት መስክ በሁለተኛ ዲግሪ ያሥለጠናቸውን 64 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ካሰመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 16ቱ ሴቶች ናቸው ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ነው። የዕለቱ ተመራቂዎች በተሰማሩበት የስራ መስክ ህዝቡን በቅንነት በማገልገል ሀገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል ። የክርስቲያን በጎ አድራጎት ማህበር ኮንሶርቲየም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ በበኩላቸው ማህበሩን በሰለጠነ የሰው ኃይል ለመገንባት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተጀመረው ትብብር አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል ። ተመራቂ ተማሪዎች ከዚህ ቀደም ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከምረቃ በኋላም አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል ። ማህበሩ በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለውን ስምምነት በማስቀጠል ለተጨማሪ የማህበሩ አባላት የትምህርት ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አመላክተዋል። ከተመራቂዎች መካከል መቅደስ ሃይሉ በሰጠችው አስተያየት ሀገሪቱ አዲስ የለውጥ ተስፋ በሰነቀችበት ወቅት መመረቋ መደሰቷን ተናግራለች፡፡ "በሰለጠንኩበት መስክ ህብረተሰቡን በታማኝነት በማገልገል ሀገራዊ የለውጥ ጉዞውን ለማስቀጠል የድርሻዬን እወጣለሁ" ብላለች ። ሌላው ተመራቂ አባይነህ ጉጆ በበኩሉ ለሀገሪቱና ለህዝቡ ተስፋን በሰጠው የለውጥ ጉዞ አሻራውን ለማስቀመጥ በትጋት እንደሚሰራ ተናግሯል።