ካናዳ የአፍርካ አገራት በአነስተኛ የካርበን ልቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታግዝ ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ካናዳ የአፍርካ አገራት በአነስተኛ የካርበን ልቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታግዝ ገለጸች
መጋቢት 10 /2013 (ኢዜአ) ካናዳ የአፍሪካ አገሮች በአነስተኛ የካርበን ልቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም የልማት ስትራቴጂን ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች።
ካናዳ ከአፍሪካ አገሮች ጋር በትብብር መሥራት የሚትችልባቸውን አማራጭ የሚያፈላልግ ስምፖዚየም ለሶስት ቀናት በበይነ መረብ ተካሂዷል፡፡
በስምፖዚየሙ ላይ ኢትዮጵያ በካናዳ -አፍሪካ የአረንጓዴ ልማት ስምፖዚየም ላይ ተሳትፋለች።
በተካሄደው ስምፖዚየም ላይ የፕላንና ልማት ኮሚሽነር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ የኢትዮጵያን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጅ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል፡፡
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመከላከል በየዓመቱ የዛፍ ተከላ እያካሄደች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአፍሪካ እየተስፋፋ ያለውን በረሃማነትን ለመግታት እና በአደጉ አገሮች ምክንያት እየደረሰ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋም እንደ ካናዳ ያሉ ያደጉ አገሮች በቴክኖሎጅና በገንዘብ የበኩላቸውን ድጋፍ እንያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል በአገራችን ያለውን የቢዝነስ ዕድሎች የሚያስተዋውቅ መድረክ ላይ የንግድና ኢንዳስትር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ልዩ አማካሪ ዶ/ር እውነቱ ሃይሉ በአገራችን ያሉትን የኢንቬስትመንት ዕድሎች፣ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጅ ላይ ማብራሪያ በመስጠት ኢንቬስተሮች ወደ አገራችን እንዲመጡ ጋብዘዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው አገራችን የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመከላከል ያሉት ተግባራት ላይ በማብራራት የአረንጓዴ ልማትና የአየር ንብረትን ለመከላከል ቀጠናዊና አለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የአከባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር ዴኤታ አህመድን መሀመድ ፣ የኢትዮዮያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመድረኩ በመሳተፍ በአረንጓልዴ ልማት ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በአነርጂ ዙሪያ የግል ባለሀብቶች በሚሳተፉበት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የመጀመሪያው ስምፖዝየም በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በከናዳ የሴኔጋል ኤምባሲና የካናዳ ውጭ ጉዳይና አለም አቀፍ ንግድ ሚኒስቴር ባዘጋጁት ስምፖዚየሙም ላይ 35 የአፍሪካ አገሮች በበይነ መረብ ተሳትፈዋል።
የካናዳ አለም አቀፍ ሚኒስትር ካርና ጉድ 132 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የካናዳ -አፍሪካ ልማት ባንክ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ለማበርከት ቃል መግባታቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡