ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተደረገ ያለው ድርድር ዓለም አቀፍ የህግ መርሆን ተከትሎ ምላሽ ማግኘት አለበት - ምሁራን

ሚዛን/ሆሳዕና መጋቢት 10/2013 /ኢዜአ/- በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅና ሱዳን ጋር እየተደረገ ያለው የሦስትዮሽ ድርድር ዓለም አቀፍ የህግ መርሆን ተከትሎ ምላሽ ማግኘት አለበት ሲሉ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብቷንና ፍትሃዊ የውሀ አጠቃቀም መርሆ በመጠቀም የምታካሂደው የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ውጤታማ ያደርጋታል ሲሉ የዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አሰታውቀዋል ።

በሚዛን ቴፒ ዩንቨርስቲ የዓለም አቀፍ ህግ መምህር ሳሙኤል ዮሐንስ ለኢዜአ እንደገለጹት "በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅና ሱዳን ጋር እየተደረገ ያለው የሦስትዮሽ ድርድር ዓለም አቀፉን የሀገራት እኩልነትና ፍትሃዊነት ህግ መሠረት ማድረግ አለበት" ብለዋል።

አደራዳሪዎች የሀገራትን የእኩልነት እንዲሁም ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ህጎችን በመጠበቅ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር አክብረው ከማደራደር ውጭ ሌላ ጉዳይ ውስጥ መግባት እንደማይጠበቅባቸው አመልክተዋል።

"አደራዳሪ አካላት የሀገራት እኩልነት ላይ የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ ህግ ካልተቀበሉና ፍትሃዊ የወንዞች አጠቃቀም ህግ ግንዛቤ የሚያንሳቸው ከሆነ ድርድሩ የህግ መርህን ያልተከተለ ይሆናል" ብለዋል።

በድርድር ወቅት ጫናዎች ሲደርሱ ኢትዮጵያዊያን ባሉበት አለም አቀፍ ህጎችን ተከትለው በመቃወም የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

"ግብጽና ሱዳን ድርድሩን አንድ ጊዜ በመበተን በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደራደር በማለት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ቀዳዳ እየፈለጉ ነው" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የፖለቲካል ሳይንስና የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ንጉስ  በላይ ናቸው።

ድርድሩን ዓለም ዐቀፍ ህግን መሠረት አድርጎ በአጭሩ መቋጨት እየተቻለ ግብጽና ሱዳን  በተደጋጋሚ በማፍረስና ባለመቀበል የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲኖርበት የማድረግ ፍላጎት እየታየባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀገራቱ በፖለቲካ ትስስር ኢትዮጵያን ከአቋሟ ለመነጠል ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ የውጭ ሀገራት እንዲያደራድሩ መፈለጋቸው  ካላቸው ፍትሃዊ የውሀ አጠቃቀም ህግን ካለመቀበል የመነጨ እንጂ ተገፍተው ያደረጉት አለመሆኑን አመልክተዋል።

"ሀገራቱ በድርድሩ ሂደት የኢትዮጵያን የውስጥ ችግር በመጠቀም አጀንዳና ሃሳብ ለማስቀየር ጥረት እያደረጉ ነው" ያሉት ዶክተር ንጉስ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮች ቢኖሩባትም እንኳ ችግሮቿ የሀገር ህልውናን ከማስጠበቅ የሚበልጡ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

"የውስጥ አንድነትን አጽንቶ መጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አሁን ያስፈልጋል" በማለት በአጽንኦት ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ንጉስ ገለጻ ኢትዮጵያዊያን ባሉበት በዬትኛውም የዓለም ክፍል በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሌሎች ሀገራት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው  በመሰራት እውነታውን ማስገንዘብ አለባቸው።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብቷንና ፍትሄዊ የውሀ አጠቃቀም መርሆ በመጠቀም የምታካሂደው የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ውጤታማ ያደርጋታል ሲሉ የዋቸሞ ዩንቨርሰቲ ምሁራን አሰታውቀዋል ።

በዩኒቨርሰቲው የህግ ትምህርት ክፍል ዲንና መምህር አቶ አሳልፈው አሰፋ እንዳሉት ግብጽና ሱዳን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት እንዳይከናወን ሀያላን ሀገራት እንዲወግኑ በማድረግ ተጽእኖ ለመፍጠር የተለያየ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን በመጠቀምና ዓለም አቀፉን ፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀም ህግ ጠብቃ የውሀ ሙሌቱን በማካሄዷ ውጤታማና ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነችበት መሆኑን አመልክተዋል ።

ሀገሪቱ የምታካሂደው የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትም በተመሳሳይ መልኩ ዓለም አቀፍ ህግና መርህን ተከትሎ የሚከናወን እስከ ሆነ ድረስ ውጤታማ እንደሚያደርጋት አመላክተዋል ።

"ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግና መርህን ተከትላ የምታካሂደው ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በፍጥነት መከናወኑ ተሰሚነቷን ያሳድጋል" ያሉት ደግሞ  በዩኒቨርስቲው የህዝብ ግንኙነትና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰብስባቸው ኃይለሚካኤል ናቸው።

ከድርድሩ ባለፈ የውሃ ሙሌቱን ስራ በተገቢው መልኩ ማከናወን የተደራዳሪ ሀገራትን ተጽዕኖ የመቀነስና ድርድሩ በሚፈለገው መልኩ እንዲሄድ ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን  አቶ ሰብስባቸው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም