ቀጥታ፡

ክልሉ የሁለቱን ሀገራት የሰላም ግንኙነት ለማጠናከር የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ ነው ---ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

መቀሌ ሀምሌ 21/2010 በኢትዮጰያና በኤርትራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው አዲስ የሰላም ግንኙነት እንዲጠናከር የሚጠበቅባቸውን  ለመወጣት የትግራይ ክልል መንግስትና ህዝብ ዝግጁ መሆናቸውን ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡ በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች መካከል የተጀመረው ሰላም ለመደገፍ የተዘጋጀ ሰልፍ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ለኤርትራ ህዝቦች ነፃነት መስዋዕትነት በመክፈል ያሳዩት ፅናት ሁሌም የሚታወስ ነው። በሁለቱም ሃገራት መካከል ላለፉት 20 ዓመታት በተፈጠረው የድንበር ውዝግብ ደግሞ በጋራ መጥፎ የታሪክ ጠባሳ ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል። በቅርቡ የተጀመረው አዲስ የሰላም ግንኙነት ለሁለቱም ህዝቦች ዘላቂ ጥቅም የሚበጅ በመሆኑ የክልሉ መንግስትና ህዝብ እንደሚያደንቁ ዶክተር ደብረጽዮን አመልክተዋል፡፡ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የክልሉ ህዝብ የሁለቱን አገራት የሰላም ግንኙነት ለማጠናከር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል። መንግስታት የሚቀያየሩ መሆናቸው ያወሱት ዶክተር ደብረጽዮን፣" ህዝብ ነዋሪና የማይተካ መሆኑን በመገንዘብ  የሰላም ጥረቱ ዘላቂ እንዲሆን የህዝብ ለህዝብ ውይይቱ በቶሎ ሊጀመር ይገባል " ብለዋል። ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ተጠብቆ  የህዝቦች አንድነትና የጋራ ጥቅም ይበልጥ እንዲከበር ብሔሮችና ብሔረሰቦች በጋራ መስራት እንዳለባቸው  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል። የሀገሪቱ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ድህነትና ኋላቀርነትን ታሪክ እንዲሆን ባሳዩት ቆራጥነት  በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ያስታወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣" ሀገራችን በፈጣን እድገት ትገኛለች "ብለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የህዳሴውን  ጉዞ  ወደ ኋላ የሚጎትቱ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች እየተከሰቱ መሆናቸውንም አመልክተው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ የመስራት ህገመንግስታዊ መብቱን መጋፋት ተገቢ እንዳልሆንም አውስተዋል፡፡ "ህገመንግስታዊ ስርዓታችን ለማፍረስ የሚደረገው ጥረት በማውገዝና የተበላሸው ሰላማችንን ለማስተካከል  ብሔሮችና ብሔረሰቦች ዋነኛ ተዋናዮች ሊሆኑ ይገባል "ብለዋል። የሀገሪቱን  አንድነትና  እድገት ዘላቂ የሚሆነው ሁሉም ህዝቦች በጋራ መነሳት ሲችሉ ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል። ዶክተር ደብረጽዮን በማያያዝም የኢንጂነር ስመኘው ድንገተኛ ሞት የክልሉ መንግስትና ህዝብ ያሳዘነ መሆኑን በመግለፅ "የተጀመረውን የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተሳትፏቸውን ያጎለብታሉ "ብለዋል። በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ በወጡት ሰልፈኞች ላይ የተፈጸመው የቦንብ ጥቃትና የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ክልሎች ባሉበትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ባካተተ መልኩ የማጣራት ሂደት እንዲካሄድና ለህዝቡ ግልጽ መረጃ እንዲሰጥም ጠይቀዋል። ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል የመቀሌ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አመተ ገብረመድህን በሰጡት አስተያየት ፣" የሰላም አስፈላጊነት ከኛው በላይ የሚያውቀው ስለሌላ ሰላማችን ሲባለሽና ሲደፈርም ተመልካች መሆን የለብንም "ብለዋል። ታጋይ የጦር ጉዳተኛው ቢንያም ብርሃነ በበኩላቸው፣የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነትና የጋራ እድገት ለማረጋገጥ ሀዝቦቻቸው ተቀራርበው በችግሮቻቸው ዙሪያ ማወያየት እንደሚገባ አመልክተዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የመቀሌ ከተማና የአካባቢዋ ነዋሪዎች  የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰንደቅ  ዓላማዎች እያውለበለቡ ባካሄዱት ሰልፍ በሁለቱ ሀገራት የተጀመረውን ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው ያላቸውን ድጋፍ በያዙት መፈክርና በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ በህገመንግስቱ ላይ እየደረሱ ያሉት ጥሰቶች እንዲቆሙና ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መሀንዲስ ሆነው የመሩት የህዳሴ ግድብ ለማስቀጠል እንደሚደግፉ አመላክተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም