ልዩነቶቻችን የጸብ መንስኤ ሊሆኑ አይገባም---ፓስተር ጻዲቁ አብዶ - ኢዜአ አማርኛ
ልዩነቶቻችን የጸብ መንስኤ ሊሆኑ አይገባም---ፓስተር ጻዲቁ አብዶ
አዲስ አበባ መጋቢት 10/2013/ ኢዜአ/ ልዩነቶቻችን የጸብ መንስኤ ሊሆኑ አይገባም ሲሉ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ ለኢዜአ እንዳሉት ህብረቱ በተለያዩ ጊዜያት ሰላም ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል።
አሁን አሁን በተለያዩ አካባቢዎች ሀይማኖትና ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸው እነዚህ ልዩነቶች ለግጭት መነሻ ሊሆኑ አይገባም ብለዋል።
ልዩነታችን ጸጋ እንጂ መርገም ሊሆን አይገባም ብለዋል።
ብዝሀነታችን የበረከት ምንጭ መሆኑን ተገንዝበን ተደጋግፈን የምናድግበት ሊሆን ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በህብረቱ የሰላምና ዴሞክራሲ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ሂርጳሳ በበኩላቸው ህብረቱ ግጭቶችን ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ አስቀድሞ እንዳይፈጠሩ የማህበረሰብ ውይይት እንዲደረግ ሲያግዝ መቆየቱን ገልጸዋል።
ለዚህ የሚረዳ ማኑዋል በማዘጋጀት በጌዲዮ፣ጉጂ፣ምዕራብ አርሲ፣ሆሮ ጉዱሩ ለሚገኙ አገልጋዮች የአሰልጣኞች ስልጠናው መሰጠቱን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈ ሴቶች በሰላም ላይ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሰላም ግንባታ ስራ የአንድ አካል ስራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም መሆኑንም አስረድተዋል።
ወጣቶች ግጭቶችን፣ ፍላጎቶቻቸውን፣ ሀሳባቸውን እንዲሁም ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚችሉበት ክህሎት እንዲኖራቸው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም አለመወያየት እና አለመደማመጥ እንዲሁም በመንፈሳዊ ስራዎች ብቻ በመጠመድ ማህበራዊ ሀላፊነቶች አለመወጣት እንደክፍተት ተለይተዋል ብለዋል።
በቀጣይ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት በእቅድ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በሰላም እሴት ግንባታ ላይ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሀፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ናቸው።
ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት መከፋፈል እንደሌለባቸው በማስተማር በኩል የሀይማኖት አባቶች ሚና የላቀ መሆኑን አንስተዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች አላስፈላጊ ዋጋ እየከፈልን ነው ያሉት ዋና ጸሀፊው አባቶች ይህን ተግባር በጽኑ ያወግዙታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ህብረት አብያተ ክርስቲያናት ህብረት 36ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ አካሂዷል።