አሜሪካ በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ተጨማሪ 52 ሚሊዮን ዶላር የሰብአዊ ዕርዳታ ማድረጓን ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ተጨማሪ 52 ሚሊዮን ዶላር የሰብአዊ ዕርዳታ ማድረጓን ገለጸች
መጋቢት 10/2013 ዓም (ኢዜአ)አሜሪካ በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ተጨማሪ 52 ሚሊዮን ዶላር የሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሀገራቸው በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ተጨማሪ 52 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እያደረገች ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ጠቁመዋል።
አንቶኒ ብሊንከን የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ላይ ለጋሽ ማህበረሰቡም አስተዋጽዎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ድጋፉ ለ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች እንዲሁም በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ እና አሁን ደግሞ መልሶ ማቋቋም ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል 153 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት በኩል መደረጉን ከአሜሪካ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
በተያያዘ አምበሳደር ፍጹም አረጋ የአሜሪካ መንግስትና ህዝብ በትግራይ ክልል ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ በመወሰናቸው አመስግነዋል፡፡
አምባሳደር ፍጹም አረጋ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እኤአ ከ1903 ጀምሮ የዘለቀ ነው ብለዋል።
የአሁኑ ድጋፍ ሌሎች የልማት አጋሮች ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ተምሳሌት የሚሆን ነው ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡