ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሕግና ደንብ መሰረት እየሰራ አይደለም...የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን

መጋቢት 9/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሕግና ደንብ ጠብቆ እየሰራ አይደለም ሲል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዝግጅት፤ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ ያለውን ቅሬታና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ቡድን ኢትዮጵያ ከምትሳተፍባቸው የስፖርት አይነቶች ዋናውና ትልቅ ውጤት የሚጠበቅበት መሆኑ ይታወቃል።

በመግለጫው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ አሰልጣኞችና አትሌቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ተሳታፊ አትሌቶች ሆቴል ገብተው ልምምድ ላይ ቢሆኑም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አትሌቶቹን በአግባቡ መንከባከብ አልቻለም ስትል ገልጻለች።

በጉድለት ከተነሱት መካከልም አትሌቶች በልምምድ ላይ እያሉ መቅረብ ካለበት ውሃ ጀምሮ በቂ ሕክምናም እያገኙ እንዳልሆነ ጠቅሳለች።

ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለአትሌቶችና ለአሰልጣኞች መክፈል የነበረበትን የላብ መተኪያ ጨምሮ የሆቴል ወጪያቸውንም በአግባቡ መክፈል እንዳልቻለ ተናገራለች።

ካለፈው ሕዳር ጀምሮ የሸፈነው የሆቴል ወጪ ከሁለት ወር ያልበለጠ ነው ስትል ጠቅሳለች።

በዚህም ምክንያት አትሌቶች ለአራት ወራት የተጠቀሙበት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሆቴል ወጪ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ባለመክፈሉ ፌዴሬሽኑ ለመክፈል ተገዷል ብላለች።

"የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በተለያዩ ጊዜያት የአሰራር ጥሰቶችን እየፈጸመ ነው" በማለት ተናግራለች ደራርቱ።

ይህን ጉዳይ ለዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሶስት ቀናት በፊት በማሳወቅ ምላሹን እየተጠባበቁ እንደሆነም ነው የገለጸችው።

የኦሊምፒክ ቡድኑ አትሌቶች ከነገ መጋቢት 10 ቀን 2013 ጀምሮ ከዚህ በፊት ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከያዘላቸው ሆቴል ለቀው በአንድ ሆቴል ተሰባስበው እንዲሰሩ ይደረጋል ብላለች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር በዛብህ ወልዴ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የአገር አቀፉ ስፖርት ማህበራት መተዳሪያ ደንብ በማይፈቀደው መልኩና ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አሰራር ውጭ የተለያዩ የሕግ ጥሰቶችን እየፈጸመ ነው ብለዋል።

በቶኪዮ 2020 ኢትዮጵያን የሚወክሉና በሆቴል የሚገኙ አትሌቶችን ለመቀነስ በማሰብ የተሳሳት መረጃ ሰጥተውናልም ነው ያሉት።

ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለአትሌቶችና አሰልጣኞች ከጥቅማጥቅም ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ብናቀርብም ጥያቄችንን መመለስ አልቻለም ያሉት ደግሞ አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሽቦ ናቸው።

ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበትና ለአንድ ዓመት ተራዝሞ በዚህ ዓመት በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ከሩጫ በተጨማሪ በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ፣ በብስክሌትና በውሃ ዋና ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም