የኢንጂነር ስመኘው የአሟሟት ሁኔታ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንጂነር ስመኘው የአሟሟት ሁኔታ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ
አዲስ አበባ ሐምሌ 21/2010 ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ ም በመስቀል አደባባይ ሞተው የተገኙት የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የአሟሟት ሁኔታ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት እና ሰማያዊ ፓርቲ በጋራ ሆነው በኢንጂነሩ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። ፓርቲዎቹ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ውጤት ቢመዘገብም በተቀራኒው ግድያዎች፣ የበርካታ ሰዎች መፈናቀል፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውሶች በተደጋጋሚ እየተከሰቱ መምጣታቸው ገልጸዋል። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ ም በመስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደሃላፊነት ከመጡ ወዲህ ለተመዘገበው ለውጥና ለመጣው አገራዊ አንድነት ዕውቅና ለመስጠት በተጠራው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተፈጸመው የቦንብ ጥቃት ተጣርቶ ይፋ ሳይደረግ መቆየቱ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም የኢንጅነሩ አሟሟት በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ በማድረግ መንግስታዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል። ኢንጅነር ስመኘው የሚመሩት ፕሮጀክት ግዙፍ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የግድቡን ግንባታ የማይፈልጉ አካላት በመኖራቸው ጥበቃና ሹፌር ሊመደብላቸው ይገባ እንደነበር ገልጸዋል። ግድቡ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተውጣጣ ገንዘብ እየተገነባ በመሆኑ ግድያው በህዝቡ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልጸው በአስቸኳይ ግድያው ተጣርቶ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግስት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ኢንጅነር ስመኘው ከቤተሰባቸው ተለይተው በበረሃ ውስጥ ሲደክሙ እንደነበር ያስታወሱት ፓርቲዎቹ የግድቡን ግንባታ በእልህና በቁጭት በማጠናቀቅ ህያውነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። ፓርቲዎቹ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ነብስ በገነት እንድታርፍ፣ ለወላጆች፣ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች፣ የሥራ ባልደረቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን ተመኝቷል።